“የሚመጡ ኢንቨስትመንቶች የማኅበረሰቡን ጨዋነት ዋስትና በማድረግ ነው” የኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ

23

ደብረ ብርሃን: ጥር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደብረ ብርሃን ከተማ ሥልጠና ሲከታተሉ የነበሩ የሦስት ዞኖች የጸጥታ ተቋማት ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች በከተማው ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።

የአማራ ክልል ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ብለዋል።

የጸጥታ ችግሩ በማምረት እና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ላይ ተጽዕኖው ከፍ ያለ ቢኾም በሕዝቡ ጨዋነት ግን ቀላል የማይባሉት የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተጥብቀው ሥራቸውን እየሠሩ ነው ብለዋል። ኀላፊው አልሚዎችም ወደ አካባቢው ሲመጡ የአካባቢውን ሕዝብ ጨዋነት በመተማመን እንደኾነ ተናግረዋል።

ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ የጸጥታ ሥራ ቀዳሚው ነው ያሉት ኀላፊው የጸጥታ መዋቅሩም ያሉትን ሃብቶች መመልክቱ ከሕዝቡ ጋር ተናቦ ጠንካራ የሰላም ሥራ እንዲሠራ ያስችለዋል ብለዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ እንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ገብረሕይዎት በከተማው እስካሁን ከ102 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 598 ኢንቨስትመንቶችን መሳብ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ 400 የሚኾኑት ኢንቨስትመንቶች ከሦስት ዓመታት ወዲህ የመጡ ናቸው። ይህ ደግሞ የአካባቢው የመልማት አቅም በፍጥነት እያደገ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል።
በከተማው ያሉት ኢቨስትመንቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ ለ130 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

88 ኢንዱስትሪዎች በምርት ላይ ናቸው ያሉት አቶ ብርሃን አሁን ላይ የአካባቢውን ጥሬ እቃ በሚጠቀሙ የኢቨስትመንት ዘርፎች ላይ በትኩረት እየሠራን እንገኛለን ነው ያሉት።
ጉብኝት ያደረጉ የጸጥታ አካላትም የኢንቨስትመንት ልማቱን ከችግር ነጻ ለማድረግ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ለዓለም ለይኩን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጎንደር ለጥምቀት መቆያ በሚኾን 14ኛው የባሕል ፌስቲባል ደምቃለች።
Next articleበከተማዋ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የደሴ ከተማ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ፡፡