
ጎንደር: ጥር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጎንደር እና ብልሃተኛ ልጆቿ የጥምቀት ድግሳቸውን አሰናድተው እንግዶቻቸውን እየተቀበሉ ነው። የጥምቀት ሰሞን ጎንደር የተገኘ ሰው ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን በግብር ተገልጠው ያያል።
ጎንደር በጥምቀት ዋዜማ በሚካሄደው 14ኛው ጥምቀትን በጎንደር የባሕል ሳምንት ፌስቲባል ደምቃለች። በፌስቲቫሉ ላይ ከጎንደር ከተማ እና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወረዳዎች የተውጣጡ የኪነ ጥበብ እና የባሕል ባለሙያዎች የተለያዩ ትርኢቶችን ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኀላፊ አበበ ላቀው ፌስቲባሉ የጎንደርን እና የአካባቢውን ባሕል፣ ቅርስ እና የሕዝቦችን እሴት ለማስተዋወቅ ያለመ ነው ብለዋል።
በፌስታቫሉ ላይ የባሕል አልባሳት፣ የኪነ-ጥበብ ውጤቶች፣ የጎዳና ላይ ትርኢት እና የፎቶ ግራፍ ኤግዚቢሽን ይቀርብበታል። የፌስቲባሉ ተካፋይ ባለሙያዎችም በየዓመቱ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። ይህ የባሕል ፌስቲባል ሁሌም ከጥምቀት በፊት የሚካሄድ ተወዳጅ ኹነት ነውም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!