
ባሕር ዳር: ጥር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ እምቢአለ በዓላቱን ምክንያት በማድረግ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የአማራ ክልል ከታኅሣሥ ወር የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ ጥርን በሙሉ ልዩ ልዩ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት እንደሚከበሩ አንስተዋል።
ጥምቀት በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ይከበራል ያሉት ኀላፊው በጎንደር፣ በባሕር ዳር እና በምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ በድምቀት እንደሚከበር ነው የተናገሩት።
ጥምቀትን ለማክበር ዝግጅት መጨረሱንም አንስተዋል። በዓሉ ከፍተኛ የኾነ ማኅበራዊ እና የምጣኔ ሃብት ትስስር የሚጨምር መኾኑንም ገልጸዋል። የጥምቀት በዓል የተቀዛቀዘውን የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃም አመላክተዋል።
አሁን ላይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እየገቡ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የቱሪስቶች መግባት ከምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳው ባለፈ የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል።
የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር እንደሚሠሩም ተናግረዋል። በዓሉ ኢትዮጵያዊ ለዛውን እንደጠበቀ መከበር ይገባዋልም ብለዋል።
የጥምቀት በዓል ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለምን ሕዝብ በመማረክ በዓለም አቀፍ ቅርስነት መመዝገቡንም አስታውሰዋል። ጥምቀት ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይገባዋልም ብለዋል።
የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ ክልሉ የሚመጡ እንግዶች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። በክልሉ ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ፣ ጥር 13 በሰከላ የግዮን በዓል፣ ጥርን በባሕር ዳር፣ ጥር 21 በመርጡ ለማርያም፣ በደረስጌ ማርያም፣ በግሸን ማርያም፣ ጥር 23 የአገው ፈረሰኞች በዓል በድምቀት እንደሚከበሩም አንስተዋል። እንግዶችን በተሟላ ሁኔታ ለመቀበል በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል።
ሁሉም የአማራ ሕዝብ እሴትን በጠበቀ መልኩ እንገዶችን እንዲቀበልም ጥሪ አቅርበዋል። በዓላቱ የሕዝብ በዓላት በመኾናቸው በዓሉም በሰላም እንዲከበር ሰላሙን መጠበቅ ይገባል። በተለመደው ጨዋነት ተቀብሎ አስተናግዶ መሸኘት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥሪ የቀረበላቸው የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያዊያን እንግዶች የአማራ ክልልን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!