
አዲስ አበባ: ጥር 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዲፕሎማሲ ሳምንት ኤግዚቢሽኑ የዲፕሎማሲ ኹኔታን በሚገባ ያስተዋወቀ መኾኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ.ር) ገልጸዋል።
አምባሳደሩ በሳምንታዊ መግለጫቸው ላይ እንዳሉት በአረብ ሊግም ኾነ በግብጽ ወደብን በተመለከተ የተሰጠው መግለጫ ትክክል አይደለም። በግብጽ የውጭ ጉዳይ በኩል የተሰጠው መግለጫ ተቀባይነት እንደሌለውም አስገንዝበዋል። አምባሳደር ዶክተር መለስ እንዳብራሩት የወደብ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የፍትሕ፣ የርትዕ እና የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እንዳለመታደል ኾኖ ወደብ የላትም፤ የዚህ ትውልድ የወደብ ጉዳይም በትክክል የተወሰነ አልነበረም ብለዋል። የወደብ ጉዳይ የቅንጦት ጉዳይ አይደለም ያሉት አምባሳደር ዶክተር መለስ በየትኛውም ጊዜ ጥያቄው እና ፍላጎቱ ሊነሳ እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡ ጥያቄውን ያልተገባ አድርጎ መመልከት ግን ጊዜው አልፎበታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የወደብ ጉዳይን የመጠየቅ መብት እንዳላትም ሊታወቅ እንደሚገባ ገልጸዋል። ሌሎች ሀገሮች እና አካላት በአካባቢው ወደብ ሲያለሙ ወታደራዊ ሰፈር ሲገነቡ የኢትዮጵያ የተለየ የሚኾንበት መንገድ የለውም ነው ያሉት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳይንስ ሙዚየም እያካሄደ ባለው የዲፕሎማሲ ሳምንት ኤግዚቢሽን የዲፕሎማሲውን እንቅስቃሴ በተገቢው ማስተዋወቅ መቻሉን ቃል አቀባዩ በሳይንስ ሙዚየም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል።
አምባሳደር ዶክተር መለስ ኤግዚቢሽኑ የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ታሪክ በማሳየት ኢትዮጵያ በአፍሪካ፣ በአፍሪካ ቀንድ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች የተጫወተቻቸውን ገንቢ ሚና ለኢትዮጵያውያን እና ለዲፕሎማሲው ማኅበረሰብ ማሳየት መቻሉን ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ በቀጣይ እኔም ለሀገሬ አምባሳደር ነኝ በማለት ቃል እየገባ ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡ ለቀጣይ የዲፕሎማሲ ሥራ ትልቅ ጉልበት የሚኾን የኅብረተሰብ ድጋፍ የተገኘበት እንደኾነም ገልጸዋል።
አምባሳደር ዶክተር መለስ በዓመታዊ የአምባሳደሮች ስብሰባ፣ በዳቮሱ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም እና በገለልተኛ ንቅናቄ አባል ሀገራት ጉባኤ የኢትዮጵያን ተሳትፎ በተመለከተ ገለጻም ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!