“ጥምቀትን በጎንደር ሲደላን የምናከብረው፤ ችግር ሲገጥመን የምንጥለው ሳይኾን ሁሌም በጉጉት እየጠበቅን በድምቀት የምናከብረው ልዩ መገለጫችን ነው” የጎንደር ከተማ ወጣቶች

20

ጎንደር: ጥር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ ወጣቶች በከተማዋ ወቅታዊ የሰላም ኹኔታ እና በጥምቀት በዓል የእንግዶች አቀባበል ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

በምክክሩ ላይ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። የውይይቱ ዓላማ ጥምቀት በጎንደር የቀደመ ድምቀቱን ጠብቆ እንዲከበር እና የሚመጡ እንግዶችን በሰላም ተቀብሎ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ያለመ ነው ተብሏል።

ጥምቀትን በድምቀት ለማክበር የሕዝቡ ሚና ከፍተኛ ነው፤ ወጣቶችም የበዓሉን ፋይዳ ጠንቅቀው በመረዳት በድምቀት ማክበር እና እንግዶችንም መቀበል እንዳለባቸው በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

በዓሉ እንዲያምር በአልባሳት ከመድመቅ በተጨማሪ እንግዶችን በተለመደው የሰው አክባሪነት እሴት ተቀብሎ ማስተናገድ እና በሰላም መሸኘትም አንዱ የአካባቢው የቆየ ልምድ ነው ብለዋል ወጣቶች።

ጥምቀት በጎንደር ለወትሮው የነበረውን መልክ ለማደብዘዝ አልባሌ ቅስቀሳ ላይ የሚገኙ አካላት ቆም ብለው ሊያስቡ እንደሚገባም ወጣቶች ተናግረዋል።

“ጥምቀትን በጎንደር ሲደላን የምናከብረው፤ ችግር ሲገጥመን የምንጥለው ሳይኾን ሁሌም በጉጉት እየጠበቅን በድምቀት የምናከብረው ልዩ መገለጫችን ነው”ሲሉ ወጣቶች ገልጸዋል።

ለጥምቀት በዓል የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረጉ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ከተማዋን ማስዋብ፣ ልዩ ልዩ የታቦት ማጀቢያ ቅርጻ ቅርጾችን መሥራት እና ሌሎችም ጥምቀትን የሚያደምቁ ሥራዎችን እያከናወኑ ስለመኾኑም በውይይታቸው ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የበዓሉ ባለቤት የኾነው ሕዝብ ለበዓሉ በሰላም መጠናቀቅ ከፀጥታ ኀይሉ ጋር በጋራ ሊሠራ ይገባል” ኮሚሽነር ደስየ ደጀን
Next article“በግብጽ እና በአረብ ሊግ በኩል የኢትዮጵያን የወደብ ፍላጎት አስመልክቶ የተሰጠው መግለጫ ተቀባይነት የለውም” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር