
ባሕር ዳር: ጥር 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት መካከል ጥምቀት አንዱ ነው፡፡ በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች ላይ ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ክብረ በዓልነቱ ባሻገር ለቱሪዝም እንቅስቃሴው የተለየ ትርጉም አለው፡፡
ክልሉ ከቆየበት የሰላም እጦት ወጥቶ የአደባባይ ሃይማኖታዊ በዓላትን ማክበር መጀመሩ የክልሉን ገጽታ በመቀየር በኩል የተጫወተው ሚናም የጎላ ነበር፡፡ ልደትን በላሊበላ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ፍፁም ሰላማዊ በኾነ መንገድ መከበሩ ትልቅ ስኬት ተደርጎ ተወስዷል፡፡
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በተለይም በጎንደር የሚከበረው የጥምቀት በዓል ፍፁም ሰላማዊ እና የተረጋጋ ኾኖ እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስየ ደጀን በየደረጃው የሚገኘው የፖሊስ መዋቅር በዓሉ በሰላም እንዲከበር የሚያስችል እቅድ አዘጋጅቶ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኙት የፖሊስ እና የፀጥታ መዋቅር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች አጠናቅቀዋል ያሉት ኮሚሽነር ደስየ በየቀጣናው የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊትም በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚያስችል በቂ ዝግጅት አድርጓል ነው ያሉት፡፡
የበዓሉን ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ለዛ እና ይዘት ለማጠልሸት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚደረገው ዘመቻ ፍጹም ተቀባይነት የለውም ያሉት ኮሚሽነሩ የጥፋት ኀይሎችን ፍላጎት ለማስፈጸም የሚሞክሩ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡ ጥምቀት በጎንደርም ኾነ በሁሉም አካባቢዎች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲከበር የሚያስችል የፀጥታ መዋቅር ቁመና ስለመኖሩም አረጋግጠዋል፡፡
“የበዓሉ ባለቤት የኾነው ሕዝብ ለበዓሉ በሰላም መጠናቀቅ ከፀጥታ ኀይሉ ጋር በጋራ ሊሠራ ይገባል ብለዋል ኮሚሽነር ደስየ ደጀን። በተለይም ወጣቶች ከዚህ ቀደም የሚታወቁበትን ግብረገብነት ሊያረጋግጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡ የፀጥታ ኀይሉን ማገዝ፣ ተናብቦ መሥራት እና የተለየ ነገር ሲያስተውሉ በአካባቢያቸው ለሚገኝ የፀጥታ ኀይል ጥቆማ በመስጠት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
