
ጎንደር: ጥር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮየጎንደር ቀሚስ፣ አልቦ፣ ድሪ፣ አምባር፣ ቀልቤ እና ሌሎችም የባሕላዊ አልባሳት እና ጌጣጌጦች በጎንደር ጥምቀት ላይ በስፉት ይታያሉ፤ የበዓሉም ድምቀት ናቸው።
እነዚህ አልባሳት እና ጌጣጌጦች ለሴቶች ሲኾኑ ወንዶች ደግሞ ጃኖ እና ሌሎች ባሕላዊ አልባሳትን ለብሰው በጥምቀት ይታያሉ። “ለጥምቀት ያልኾነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እንደሚባለው አልባሳት እና ጌጣጌጦቹ ለጥምቀት ጎልተው ይታዩ እንጅ በሌሎች በዓላትም መድመቂያ ናቸው።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ለጎንደር ጥምቀት ልዩ ውበት የኾኑትን የባሕላዊ አልባሳት ገበያ ተዘዋውሮ ቃኝቷል። በጎንደር ከተማ አራዳ ገበያ ውስጥ እግር ጥሎት የገባ ሰው በጃኖ እና በጎንደር ቀሚስ የደመቁ በርካታ የአልባሳት ሱቆችን ይመለከታል።
በተለይም በጥምቀት በዓል መዳረሻ የአልባሳት ገዥ እና ሻጭ በስፋት ይገናኛሉ። በአራዳ ገበያ ውስጥ ያነጋገርናቸው ገዥዎች ያለ ባሕል አልባሳት ጥምቀት አይደምቅም የሚል ሃሳብ አላቸው።
የባሕል አልባሳቱ ገበያ ሙሉ ስለመኾኑም ገዥዎች ገልጸዋል። የዋጋው ሁኔታ ከባለፈው ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ጭማሪ እንዳለውም አንስተዋል። ለአብነትም መካከለኛ ደረጃ ያለው የጎንደር ቀሚስ ሲሸጥ ተመልክተናል። ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የአንድ ሺህ ብር ጭማሪ እንዳለው ገዥዎች ገልጸውልናል። የባሕል አልባሳቱን በቡድን የሚገዙ በርካቶች ናቸው።
ያነጋገርናቸው የባሕል አልባሳት ሠሪዎች እና ነጋዴዎችም መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ስለመኖሩ ተናግረዋል። ይህም ወቅታዊ ሁኔታው የፈጠረው ጭማሪ ነው ብለዋል። የባሕላዊ አልባሳት ዋጋ በየባዕላቱ የሚደራ ቢኾንም የጥምቀት ግን ልዩ ነው ይላሉ ነጋዴዎች።
የባሕል አልባሳት ገበያ ወዲህ በርካታ የሥራ እድል የሚፈጥር፣ ወዲያ ደግሞ በራስ ቀለም የሚያደምቅ ስለመኾኑ ነጋዴዎች ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!