“ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓለ ጥምቀቱን ሲያከብር ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ሊኾን ይገባል” የባህር ዳር ሀገረ ስብከት

20

ባሕር ዳር: ጥር 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝበ ክርስቲያኑ የከተራና የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ሃይማኖታዊ ሥርዓቱንና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ሊሆን ይገባል ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተናገሩ።

በዓለ ጥምቀቱ በባሕርዳር ከተማ ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል። ዋና ሥራ አስኪያጁ መላከ ሰላም ኤፍሬም ሙሏለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ዕምነቱ በሚያዘው መሰረት በሰላምና በፍቅር ሊሆን ይገባል።

በዓሉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ በአንድነትና በመተሳሰብ በድምቀት ተከብሮ እንዲውልም የሰላም፣ የመድረክ አስተባባሪና ሌሎች ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሲሰሩ መቆየታቸውን አውስተዋል።

በከተራው ዕለት በባሕር ዳር ከተማ ከሚገኙ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማትና አድባራት የሚወጡ ታቦታት ወደ ማደሪያ ቦታቸው በዝማሬና በእልልታ ታጅበው ወደ ማረፊያ ስፍራው ይደርሳሉ ብለዋል።

ለዚህም አባቶች፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ የወጣቶች ኅብረትና ከፅዋ ማኅበራት የተውጣጡ በዓሉ በሰላም እንዲከበር በሚያስችል መልኩ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል።

ሁሉም የዕምነቱ ተከታዮች የበዓሉ ዋና ባለቤቶች መሆናቸውን ተገንዝበው በሰላምና በፍቅር ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የጥምቀት በዓልን በዝማሬ፣ በምሥጋናና በእርጋታ በማክበር ታቦታቱ ካደሩበት ባሕረ ጥምቀት ወደ መንበራቸው በሰላም እንዲገቡም ተገቢውን እገዛ ማድረግ እንደሚገባም መልክዕት አስተላልፈዋል።

በባሕር ዳር ከተማ የሚከበረው በዓሉ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በጣና ዳርቻ በድምቀት እየተከበረ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። ኢዜአ እንደዘገበው ሕዝበ ክርስቲያኑም ኢትዮጵያዊ ባሕልና እሴቱን በጠበቀ መልኩ በመፈቃቀርና በመተሳሰብ በዓሉን እንዲያከብርም መላከ ሰላም ኤፍሬም ሙሏለም አስገንዝበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ደመቀ መኮንን ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን መስራች እና ሊቀ መንበር ቢል ጌትስ ጋር ተወያዩ።
Next article“በክልሉ የተፈጠረውን ቀውስ ወደ ቀደመ ሰላም ለመመለስ የፀጥታ ኃይሉን አቅም በሥልጠና የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል” የአማራ ክልል ሰላም እና ደኅንነት ቢሮ