
ደብረ ብርሃን: ጥር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ በዞኑ 2 ሺህ 932 የማኅበረሰብ ተፋሰሶችን በመለየት ከሰው እና እንሰሳት ንክኪ ተጠብቀው እንዲቆዩ መደረጉን አስታውቋል፡፡
የመምሪያው ኀላፊ ታደሰ ማሙሻ እንዳሉት 1 ሺ 641 ተፋሰሶች ወደ ልማት መግባታቸውንም አስረድተዋል፡፡ 432 ይዞታዎች ከልቅ ግጦሽ ነጻ ኾነው የተሻለ የተፈጥሮ ገጽታን ተላብሰው እንደሚገኙ ኀላፊው ተናግረዋል ።
መምሪያ ኀላፊው በተፈጥሮ ሃብት ላይ የደን መመንጠር እና ሕገ-ወጥ ግጦሽ ጉልህ ተጽእኖ እያሳደሩ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት። የግብርና ሥራን ለመደገፍ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ወሳኝ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡
በዞኑ ከ459 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተፈጥሮ ሃብት ልማቱ ተሳትፎ ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በዚህ ዓመት በሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ከ31 ሺህ 200 ሔክታር በላይ መሬት ይሸፈናል ተብሏል። የተፈጥሮ ሃብት ሥራው በገንዘብ ሲተመን ከ604 ሚሊዮን ብር በላይ ይኾናል ተብሎም ይገመታል፡፡ ጥር 20/2016 ዓ.ም ላይ በዞኑ አጠቃላይ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ በይፋ እንደሚጀመርም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፡- ስንታየሁ ኃይሉ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!