
ባሕር ዳር: ጥር 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጥምቀትን በጎንደር በድምቀት ለማክበር ከሕዝብ ጋር የተቀናጀ ዝግጅት ማድረጉን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ገልጿል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያም የ2016 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን በጎንደር ከተማ ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ እና በሰላም ለመሸኘት ዞኑ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
“ጥምቀት በጎንደር ልዩ መገለጫችን ነው፤ እንኳንስ ኢትዮጵያዊ ሰው የመላው ዓለም ሕዝብ ጭምር በዓሉን በጉጉት ይጠብቀዋል” ሲሉም ተናግረዋል።
በዓሉን ልክ እንደወትሮው በድምቀት ለማክበር ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሆቴሎች፣ ከወጣቶች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ ውይይቶች መደረጋቸውንም ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ እንግዶችን እንደየፍላጎታቸው ለማስተናገድም ሙሉ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት። ከአሁኑ ጀምረው በርካታ እንግዶች እየገቡ መኾኑን የገለጹት አቶ ወርቁ የጥምቀት ድምቀት እንዲደበዝዝ በማሰብ በርካታ ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት ድርጊታቸው ኀላፊነት የጎደለው መኾኑን ተገንዝበው ከእንዲህ አይነት አካሄዳቸው እንዲታረሙ አሳስበዋል።
ይህንን ውብ የሕዝብ ሃይማኖታዊ በዓል ከአልባሌ የፖለቲካ እሳቤ ጋር ማደበላለቅ ውበቱን የሚቀንስ መኾኑን መገንዘብ እንደሚገባም ጠቁመዋል። የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የጸጥታ ዝግጅት መደረጉንም ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል። ከምንም በላይ ግን በዓሉ የሕዝብ የኾነ እና በዓለም ቅርስነትም የተመዘገበ ሃብት መኾኑን ታሳቢ አድርጎ መላው ሕዝብ በጸጥታው ሥራ ላይ መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል።
ጥምቀትን ለማክበር የሚመጡ እንግዶች እግረመንገዳቸውን በጎንደር እና አካባቢው የሚገኙ በርካታ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን ተዘዋውረው መጎብኘት እንደሚችሉም የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!