”ያለንን ከማካፈል ይልቅ ችግር እየጨመሩ ኅብረተሰቡን ማሰቃየት ከባሕላችንም ከታሪካችንም ያፈነገጠ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

39

ባሕር ዳር: ጥር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ እና ሸማች ተኮር የግብይት ሥርዓትን ለመገንባት ከአጋር አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

የውይይቱ ዓላማ ሕገ ወጥነትን በመከላከል ጤናማ የንግድ ሥርዓት በመፍጠር፣ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም እና ዋጋን በማረጋጋት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደኾነ ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መኾኑን በመገንዘብ አሥተዳደራቸው ችግሩን ለመፍታት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

የሸማች ማኅበራት እና ዩኒየኖች የ60 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጎላቸው ሥራ መጀመራቸውንም ተናግረዋል። ባንኮች ችግሩን ለመቋቋም ያሳዩትን የትብብር መንፈስ ያበረታቱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አብሮ ለመሥራት ፈቃደኛ የኾኑ ባለሃብቶችንም አመሥግነዋል።

”ያለንን በማካፈል ችግሩን ከማለፍ ይልቅ ከችግር ላይ ችግር እየጨመርን ኅብረተሰቡን ማሰቃየት ከባሕላችንም ከታሪካችንም ያፈነገጠ ነው” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሕገ ወጥነቱ እንዲታረም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ብዙዓየሁ ግዛቸው የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ እና ለማረጋጋት ቢሯቸው እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

👉 ሸማች ተኮር የምርት እና ግብይት ሥርዓት መፍጠር፣
👉 የገበያ ተዋናዮችን አቅም ማሳደግ፣
👉 ሸማች እና አምራች በቀጥታ የሚገናኙባቸው ገበያዎችን ማስፋት
👉 ገበያን ዘመናዊ እና ሕጋዊ የማድረግ ሥራ እየሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።

የግሽ አባይ ሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበር ሠብሣቢ ነጮ በየነ ወቅቱን የጠበቀ ባይኾንም የከተማ አሥተዳደሩ ብር ለቅቆልን መሰረታዊ ሸቀጦችን ማቅረብ ጀምረናል ብለዋል።

በተለቀቀው ገንዘብ ጤፍ፣ ማካሮኒ፣ ፓስታ እና ሳሙና ማከፋፈል መጀመራቸውንም ገልጸዋል። የሚለቀቀው የገንዘብ መጠን ማነስ፣ ቶሎ የሚመለስ መኾኑ እና የመዘግየቱን ችግርም አንስተዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም በመድረክ የሚናገሩትን ያህል ለተግባራዊነቱ እንዲሠሩ አሳስበዋል።

የስኡዲ ጠቅላላ አስመጪ እና ላኪ ድርጅት ባለቤት መሐመድ ካሳው “የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የአማራ ክልል ባደረገልን ጥሪ መሰረት ወደ ክልሉ ገብተን መሥራት ጀምረናል” ብለዋል። ማንኛውንም የምግብ ፍጆታ ከፋብሪካዎች እና አምራቾች ተቀብለው በተመጣጣኝ ዋጋ እያከፋፈሉ መኾኑንም ተናግረዋል። ምርት ሳይጠፋ በመደበቅ የሚፈጠርን የኑሮ ውድነት ችግር የሚፈታ ሥራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በ150 ሚሊዮን ብር ወጭ የለሙ አረንጓዴ ቦታዎች እስከ የካቲት /2016 ዓ.ም ለሕዝብ ክፍት ይኾናሉ” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር
Next articleጥምቀትን በጎንደር በድምቀት ለማክበር ከሕዝብ ጋር የተቀናጀ ዝግጅት ማድረጉን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ገለጸ።