“በ150 ሚሊዮን ብር ወጭ የለሙ አረንጓዴ ቦታዎች እስከ የካቲት /2016 ዓ.ም ለሕዝብ ክፍት ይኾናሉ” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር

17

ባሕር ዳር: ጥር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ድርጅቶችን እና ማኅበረሰቡን በአረንጓዴ ልማት ለማሳተፍ እየተሠራ መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳት እና ውበት ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

በከተማ አሥተዳደሩ “በ150 ሚሊዮን ብር ወጭ የለሙ አረንጓዴ ቦታዎች እስከ የካቲት /2016 ዓ.ም ለሕዝብ ክፍት ይኾናሉ” ተብሏል። ባሕር ዳር ከተማ በጣና እና በዓባይ ወንዝ የተከበበች ብትኾንም ባላት ሃብት ልክ ሳትለማ ቆይታለች፡፡ የከተማዋ ውበት የኾኑትን ዓባይ እና ጣናን በማልማት የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ ማስፋት ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳት እና ውበት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሃም ወርቁ ገልጸዋል፡፡

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በ150 ሚሊዮን ብር ወጭ በ 8 ነጥብ 7 ሔክታር መሬት ላይ የዲፖ ክፍል አንድ እና ሕዳር 11 አካባቢ የአረንጓዴ ልማት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ የቲያትር፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የማንበቢያ፣ የተለያዩ መርሐ ግብሮችን ለማዘጋጀት እና ባሕልን ለማስተዋወቅ የሚያገለግሉ ቦታዎችን ያካተቱ መኾናቸውን ገልጸዋል። እስከ የካቲት /2016 ዓ.ም ለሕዝብ ክፍት ይኾናሉም ተብሏል።

የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የከተማዋን ውበት ከመጠበቅ ባለፈ የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ያራዝማል፤ እስከ አሁንም ለ120 ወጣቶች በቋሚነት አና በጊዜያዊነት የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በቀጣይ ወደ ተሟላ ሥራ ሲገቡ ደግሞ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል የመፍጠር አቅም አላቸው፡፡

በዚህ ዓመትም የዲፖ ክፍል ሁለት ፕሮጀክት እስከ አቫንቲ ሆቴል ያለውን ቦታ ለማልማት ጨረታ መውጣቱን ገልጸዋል፡፡ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ በጀትም ተይዞለታል፡፡ በበጀት ዓመቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ከአየር ማረፊያ እስከ አጅፕ እና ከመድኃኒዓለም እስከ አዲሱ ድልድይ የሚገባ ዋና ዋና የመንገዶችን፣ አካፋዮችን እና የመንገድ ዳር ቦታዎችን ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ ለመሥራት የዲዛይን እና የውኃ አማራጭ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ 13 ማኅበራት ተደራጅተው የአረንጓዴ ልማት ሥራ እንዲሠሩ መደረጉንም ነው የገለጹት፡

በቀጣይም ማኅበረሰቡ ከመኖሪያው እስከ 20 ሜትር፣ ድርጅቶች ደግሞ እስከ 50 ሜትር እንዲያለሙ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ደግሞ በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች እና ባለሃብቶች በዋና ዋና መንገዶች ልማት ላይ እንዲሳተፉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከተማዋን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ማኅበረሰቡ ከግቢው ጀምሮ ለጽዳት እና ውበት ሥራ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተፈጥሮን መንከባከብ የነገዋን ኢትዮጵያ መንከባከብ ነው” ተማሪዎች
Next article”ያለንን ከማካፈል ይልቅ ችግር እየጨመሩ ኅብረተሰቡን ማሰቃየት ከባሕላችንም ከታሪካችንም ያፈነገጠ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው