“ተፈጥሮን መንከባከብ የነገዋን ኢትዮጵያ መንከባከብ ነው” ተማሪዎች

5

ባሕር ዳር: ጥር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ወረዳ ቄባ ቀበሌ በጸመናቁ ተፋሰስ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ተጀምሯል። በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራው የተገኙት የቄባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ለሀገር ልማት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ተማሪ ዓለምነው ደባሽ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሲኾን “ተፈጥሮን መንከባከብ የነገዋን ኢትዮጵያ መንከባከብ ነው” ብሏል። በትምህርት ቤታቸው የአረንጓዴ አሻራ ክበብ በመመስረት እጽዋት እያለሙ እንደኾነ የገለጸው ተማሪ ዓለምነው ማኅበረሰቡም የተፈጥሮ ሃብትን በማልማት የተራቆተችውን መሬት አረንጓዴ ሊያለብሱ ይገባል ብሏል።

ተማሪ አጸደ አበባውም ማኅበረሰቡ ለምነቷ የተጠበቀች መሬትን እንጂ የተራቆተች መሬትን ሊያወርሰን አይገባም ብላለች። “መምህራኖቻችን ስለተፈጥሮ ሃብት በሳይንስ ትምህርት በደንብ ያስተምሩናል፤ ለዚህም ነው ከተፈጥሮ ሃብት ልማት ላይ ለመሳተፍ የተገኘነው” ስትል ተማሪ አጸደ ገልጻለች።

የቄባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሳይንስ መምህሩ ተክላት ዘውዱ ተማሪዎች የተፈጥሮ ሃብትን ፋይዳ እንዲያውቁ በሳይንስ ትምህርት እና በአካባቢህን እወቅ ክበብ በቂ ግንዛቤ እየፈጠርን ነው ብለዋል።

በትምህርት ቤትም ለማኅበረሰቡ ማሳያ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት መምህሩ የዋግኽምራ ማኅበረሰብም ተጀምሮ የሚቀር ሳይኾን ለዘለቄታዊ ውጤት ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። የተፈጥሮ ሃብት ልማት መርሐ ግብሩ ላይም የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ 12 ሜትር የእርከን ሥራ በመሥራት የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የትብብር እና አጋርነት ሰነድ በጋራ መልማትን የሚያረጋግጥ ነው”ዲማ ነግዎ (ዶ.ር)
Next article“በ150 ሚሊዮን ብር ወጭ የለሙ አረንጓዴ ቦታዎች እስከ የካቲት /2016 ዓ.ም ለሕዝብ ክፍት ይኾናሉ” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር