“ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የትብብር እና አጋርነት ሰነድ በጋራ መልማትን የሚያረጋግጥ ነው”ዲማ ነግዎ (ዶ.ር)

22

ባሕር ዳር: ጥር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በቅርቡ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው ሁሉን አቀፍ የትብብር እና አጋርነት ሰነድ በጋራ መልማትን የሚያረጋግጥ መኾኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳ ዲማ ነግዎ (ዶ.ር) ገለጹ፡፡

ዶክተር ዲማ በፈረንሳይ ፓርላማ የሀገር መከላከያ እና የጦር ኃይሎች ኮሚቴ ሰብሳቢ ቶማስ ጋሲሉድ የተመራውን ልዑክ ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ ዶክተር ዲማ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ሁሉን አቀፍ የትብብር እና አጋርነት ሰነድ በጋራ መልማትን የሚያረጋግጥ ሰነድ መኾኑን ለቡድኑ አብራርተዋል፡፡

ለረጅሙ ሀገራዊ እና የምጣኔ ሃብታዊ ደኅንነት በሰጥቶ መቀበል መርህ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረሰው ሁሉን አቀፍ የትብብር እና አጋርነት ስምምነት ሰነድ በጋራ ለመልማት ሚናው ከፍተኛ መኾኑን አስረድተዋል፡፡

ሰነዱን በተመለከተ በቅርቡ የአውሮፓ ሕብረት የተዛባ አስተያየት ማንፀባረቁን እና በሕብረቱ የተሰጠው አስተያየት ትክክል እንዳልሆነ የፈረንሳይ መንግስት እንዲገነዘበው ለልዑኩ ጠቁመዋል።

የባሕር በሩ አካባቢ ጸጥታ የኢትዮጵያን አስተዋጽዖ እንደሚጠይቅ የገለጹት ሰብሳቢው የተፈረመው የትብብር እና አጋርነት ሰነድ ወደ ተግባራዊ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ፈረንሳይ የበኩሏን እገዛ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡

ከምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በፈረንሳይ ፓርላማ የሀገር መከላከያ እና የጦር ኃይሎች ኮሚቴ ሰብሳቢ ቶማስ ጋሲሉድ በበኩላቸው ፈረንሳይ በማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ዘርፎች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ዝግጁ መኾኗን ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በተፈጥሮ ሃብት ልማት በዚህ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማግኘት እየሠራን ነው” የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር
Next article“ተፈጥሮን መንከባከብ የነገዋን ኢትዮጵያ መንከባከብ ነው” ተማሪዎች