“በተፈጥሮ ሃብት ልማት በዚህ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማግኘት እየሠራን ነው” የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር

7

ሰቆጣ: ጥር 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተፈጥሮ ሃብትን ማልማት ከድህነት ለመላቀቅ ወሳኝ ሚና ያለው መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሡ ወልዴ ገልጸዋል። የተፈጥሮ ሃብት ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በሰቆጣ ወረዳ 023 ቀበሌ ጸመናቁ ተፋሰስ ተከናውኗል።

በመርሐ ግብሩ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሡ ወልዴ “ባለፉት 30 ዓመታት የተፈጥሮ ሃብትን በዘመናዊ አሠራር ባለማልማታችን ከድህነት መውጣት አልቻልንም” ብለዋል።

ከችግሩ ለመውጣት የተፈጥሮ ሃብት ልማትን በዘመነ መንገድ ማልማት ያስፈልጋል ያሉት ኀላፊው በዘንድሮው ዓመትም በ409 ተፋሰስ 32 ሺህ በላይ ማኅበረሰብ በልማቱ ይሳተፋል ነው ያሉት።

የሰቆጣ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ወርቁ በወረዳው ባለፉት ዓመታት ሁለት ተፋሰሶች በተፈጥሮ ሃብት ሥራ የተለየ ተሞክሮ እና ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዓመት ደግሞ አምስት ተፋሰሶችን በማልማት ለማኅበረሰቡ የተሻለ ውጤት እንዲያስገኙ እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።

በወረዳው 62 ነባር እና 4 አዲስ ተፋሰሶችን በማልማት ባለፉት ዓመታት የታጣውን ምርት ለማግኘት በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አብራርተዋል። የሰቆጣ ወረዳ ቄቫ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አማረ መኮነን ባለፉት ሁለት ዓመታት ማሳቸውን በእርከን በማልማታቸው የተሻለ ምርት እንዳገኙ ገልጸዋል። በዚህ ዓመትም በሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ መሬታቸው ላይ እርከን በመሥራት አፈሩን ለመጠበቅ እንደሚሠሩም ነው የገለጹት፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት ቸኮለ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ለእንሰሳት መኖ እና በንብ እርባታ የተሻለ ውጤት ስለሚያስገኝ ሥራው ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡

በሰቆጣ ወረዳ ቄቫ ቀበሌ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር የተካሄደ ሲኾን በፕሮግራሙ ላይ የዞን እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የቄቫ ቀበሌ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleትምህርት ሚኒስቴር በድጋሚ የሚሰጠውን የመውጫ ፈተና መርሐ ግብር ይፋ አደረገ፡፡
Next article“ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የትብብር እና አጋርነት ሰነድ በጋራ መልማትን የሚያረጋግጥ ነው”ዲማ ነግዎ (ዶ.ር)