
ባሕር ዳር: ጥር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ወራት ሄደው ዓመት እስኪተካ ድረስ ይጓጉለታል፤ ቸር አክርመን እያሉ ይሳሱለታል፤ ቀናትን ከሳምንታት፣ ሳምንታትን ከወራት ጋር እያስተካከሉ የጊዜውን መድረስ ይጠብቁታል፡፡ ቀናት አልፈው፣ ሳምንታት ተከታትለው፣ ወራት ተሰካክተው ዓመት በደረሰ ጊዜ ደስታ እና ፌሽታ፣ ፍቅር እና መድኃኒት ያገኙበታልና፡፡
ያቺ ታሪካዊት እመቤት፣ ነገሥታቱን ያነገሰች፣ መኳንንቶቿን የሾመች፣ መሳፍንቶቹን ያከበረች፣ የጦር አበጋዞቿን ከፍ ከፍ ያደረገች፣ ሊቃውንቶቿን በምስጢር ያራቀቀች፣ እርሷም በዘመናት መካከል ንግሥት ተሰኝታ የኖረች፣ ትናንትን ከትናንትና ወዲያ፣ ዛሬን ከነገ ጋር ያስተባበረች፣ በክብሯ እና በልኳ ያለች ሥፍራ ደግሞ ጥምቀትን አብዝታ ታስናፍቀዋለች፡፡
ደግ አባት፣ ብልህ እናት ልጆቻቸው የሚኮሩበትን፣ ዘመናት አልፈው ዘመናት በተተኩ ቁጥር የሚመኩበትን፣ ለትውልድ ሁሉ በኩራት የሚያሳዩትን ውርስ ጥለው ያልፋሉ፡፡
ውርሳቸው ዘመናት የሚያደበዝዙት፣ የእድሜ ብዛት የሚያስረሱት፣ እንዳልነበር የሚያጠፉት አይደለም፡፡ ሁልጊዜም አዲስ እንደኾነ ይኖራል፤ ረቂቅ እንደኾነ ይቀመጣል እንጂ፡፡ በዚያች ሥፍራ አያሌ ነገሥታት ቅብዓ መንግሥት ተቀብተው፣ በትረ መንግሥት ጨብጠው፣ የተዋበ ዘውድ ደፍተው፣ በእንቁ ያጌጠ ካባ ደርበው፣ በወርቅ ዙፋን ላይ ተቀምጠውባታል፤ ከጊዜ የቀደመ፣ ከዘመናቸው የረዘመ ታሪክ ሠርተውባታል፡፡
የተወደደች ሀገራቸውን ኮርተው አኩርተዋታል፤ የልጅ ልጅ የሚኮራበትን ረቂቅ ጥበብ፣ ድንቅ አሻራ፣ የገዘፈ ታሪክ አስቀምጠውባታል፤ ጡብ ደርድረው የረቀቁ አብያተ መንግሥታትን፣ እጹብ የሚያሰኙ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸውባታል፤ ሕግና ሥርዓትን አስቀምጠውባታል፤ ለሁሉም፣ በሁሉም የተገባውን ፈጽመውባታል፡፡ ሊቃውንቱ ነፍስ እና ስጋን የሚያስማማ፣ በሰማይ እና በምድር የሚሰማ የአምላክ ቃልን እንደ አፍላግ አፍስሰውባታል፤ ለደቀማዛሙርታቸው አጠጥተውባታል ጎንደር፡፡ የነገሥታቱ እና የሊቃውንቱ ከተማ፡፡ በዚያች ከተማ የጦር አበጋዞች ከልባቸው ላይ ታጥቀው ሀገር ጠብቀዋል፤ ነጻነትን የተጎናጸፈች ሀገር አቆይተዋል፡፡
ተናፋቂው ጥምቀት በዚህች ታሪካዊት እመቤት ይደምቃል፡፡ ወረኃ ጥር በደረሰ ጊዜ የጎንደር ጎዳናዎቿ ይዋባሉ፣ ደጋጎቹ እንግዶቻቸውን ለመቀበል አዳራሻቸውን ያሰማምራሉ፣ እልፍኞቻቸውን ያስውባሉ፣ እንግዶች በመጡ ጊዜ እግራቸውን እያጠቡ ይቀበላሉ፣ ስሞት አፈር ስኾን እያሉ ያበላሉ ያጠጣሉ፤ መኝታቸውን እየለቀቁ ያሳርፋሉ፡፡
ለዚያም ይመስላል ከያኒው፡-
“ይመስክር ይናገር ጎንደር የሄደ ሰው
ራሱ ጦሙን ያድራል አጥግቦ እንግዳ ሰው
መሬት ጋደም ይላል አልጋ አንጥፎ ለሰው
መንግሥተ ሰማያት ገነትን ያውርሰው
ጻዲቁ ወገኔ ደጉ የጎንደር ሰው” ብሎ የተቀኘው፡፡
እንግዳ መቀበል፣ ተቀብሎ ማቀማጠል ባሕሪያቸው እና መገለጫቸው ነው፡፡ ጎንደር በጥምቀት ትደምቃለች፡፡ በጥምቀት ትዋባለች፤ ትሞሸራለች፡፡ ለዛ ባለው ውበት ታጌጣለች፡፡
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ዮናስ ይትባረክ የበዙት ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ዳራዎች፣ የከበሩ እሴቶች፣ ሥርዓቶች ጥምቀትን በጎንደር ልዩ ያደርጉታል ይላሉ፡፡ በቀደመው ዘመን 44 ታቦታት ያሏት፣ ከአርባ አራቱ አድባራት አርባ አራት ታቦታት የሚወጡባት፣ አሁን ግን የበዙ ታቦታት ያሏት ጎንደር ጥምቀትን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን፣ ታሪካዊ እውነቱን፣ የከበረ ባሕሉን እና እሴቱን አስተባብራ፣ ለሁሉም መልክና ጌጥ ሰጥታ ታከብረዋለች፡፡
በጎንደር በወረኃ ጥር የመጀመሪያዎቹ ቀናት ጀምረው ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይከወናሉ፡፡ ጥምቀት በደረሰ ጊዜ ደግሞ ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ ጎንደር በነጭ መብሩቅ የተሸፈነች መሰቦ ወርቅ፣ የሰላም እርግቦች የሚያርፉባት ዛፍ ትመስላለች፡፡ ለምን ቢሉ በልብሰ ተክህኖ የተዋቡ ጳጳሳት፣ መነኮሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ በነጫጭ ልብስ ያማሩ ምዕመናን፣ ወይዛዝርት እና ጎበዛዝት ይሠባሠቡበታል፤ በአብያተ መንግሥታት፣ በአብያተ ክርስቲያናቷ፣ በእልፍኞቿ እና በጎዳናዎቿ ይረማመዱባታልና፡፡
ከጥምቀት ዋዜማ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ ጎንደር ከዳር ዳር በምሥጋና፣ በእልልታ እና በውዳሴ ትመላለች፡፡ በኅብረት በሚወጡ ድምጾች ትደምቃለች፡፡ በእርግጥ በጎንደር ሰማይ ሥር በሰርክ ስብሐት ሳይደረስ፣ አምላክ ሳይወደስ ውሎ አያውቅም፡፡ በጥምቀት ዋዜማ ካህናቱ ወደየአድባራቱ ይጓዛሉ፣ በየአድባራቱም ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰው በቤተ መቅደስ ለአምላክ የተገባውን ምሥጋና ያቀርባሉ፤ ምዕመናኑም የሰላም መልእክተኛ እርግብ እየመሰሉ፣ በነጫጭ ልብስ እየተዋቡ፣ ወደ አብያተ ክርስቲያናቱ ይተማሉ፤ በየአድባራቱ እና በየገዳማቱ አጸድ ሥር ይሠባሠባሉ፤ በዚያም ሥፍራ በአንድነት ለአምላካቸው ምሥጋና ያቀርባሉ፡፡ በቤተ መቅደስ ያለው ሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ታቦታቱን ከመንበራቸው አውጥተው በታላቅ አጀብ ወደ ጥምቀተ ባሕር ያቀናሉ፡፡
የጎንደር ጥምቀተ ባሕር ታላቁ ንጉሥ አጼ ፋሲል አሳምረው ያሠሩት፣ በረቀቀ ጥበብ የሞሸሩት፣ ለልጅ ልጅ ይኾን ዘንድ ያረቀቁት ድንቅ ሥፍራ ነው፡፡ በዚያ ሥፍራ ውስጥ ሁሉ የተሠራው በምክንያት ነው፡፡ በዚያ ጥምቀተ ባሕር ውስጥ ታቦታት ያድራሉ፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በሊቃውንት ይፈጸማሉ፡፡
ጎንደር ሥርዓተ ጥምቀትን የምትፈጽምበት ሥፍራ ከሌሎች አካባቢዎች ልዩ ያደርጋታል ብለውናል መምሪያ ኀላፊው፡፡ በዚያ ልዩ የኾነ ታሪካዊ ሥፍራ ሊቃውንቱ የሚያቀርቡት ዝማሬ እና ዝማሜ ጥምቀትን በጎንደር የተዋበ ያደርገዋል ነው የሚሉት፡፡ አጸድ እና አጸዳቸው የገጠሙ አብያተ ክርስቲናት ያሉባት፣ እንድ እርምጃ በተራመዱ ቁጥር ሁሉ ታሪክ የሚነገርባት፣ ታሪካዊ ሥፍራዎች የሚገኙባት ጎንደር ተናፋቂ ትኾናለች፡፡ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችም ጎንደርን ለጥምቀት ይመርጧታል፡፡ ከተማ አሥተዳደሩ ከጥንት ጀምሮ በነገሥታቱ፣ በመኳንንቱ፣ በመሳፍንቱ፣ በሊቃውንቱ እና በምዕመናኑ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ታሪክን ከመንገር፣ ሃይማኖትን ከማስተማር ባሻገር ሀብት እያፈሩበት መኾኑንም ነግረውናል፡፡ ጥምቀት በጎንደር ሲከበር ጥቅሙ ብዙ ነውና፡፡
ጥምቀትን በጎንደር ማክበር የተጎዳውን ቱሪዝም ለመጠገን እና ገቢያቸውን በቱሪዝም ላይ ለመሠረቱ ወገኖች ፋይዳው ላቅ ያለ መኾኑንም ነግረውናል፡፡ ጥምቀት በጎንደር እንደ ወትሮ ሁሉ ልቆ እና ደምቆ ይከበር ዘንድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ ናቸው ነው ያሉት፡፡ ጎንደር ሰላሟን ጠብቃ የአጼ ቴዎድሮስን የልደት በዓል ማክበሯንም አስታውሰዋል፡፡
ሁልጊዜ እንደሚደረገው ሁሉ የጎዳና ላይ የባሕል ትርኢት ጥር 9/2016 ዓ.ም እንደሚኖር ነው የተናገሩት፡፡ የቱሪስቱን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም እየተሠራ ነውም ብለውናል፡፡ በዓሉ እንደ ቀደመው ሁሉ ይከበራል፤ የጸጥታ ችግርም የለም፤ እንግዶች ወደሚናፍቋት ከተማ፣ ለሚናፈቀው የጥምቀት በዓል ይምጡ፣ በተባረከው በዓል ይባረኩ፣ አትስጉ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ደምቆ ይከበራል ነው ያሉት፡፡
ጥምቀትን በጎንደር ይጓጉለታል፤ በደረሰም ጊዜ ሃይማኖቱን ጠብቀው ያከብሩታል፤ በጥምቀት ከበደል መፈታትን፣ ከደዌ መፈወሰን እንደሚያገኙበት አጥብቀው ያምኑበታልና፡፡ ያቺ ታሪካዊት እመቤት እልፍኟን አስፍታ እየጠበቀች፣ ጎዳናዎቿን አሳምራ ኑ እያለች ነው፡፡ ሂዱ በዚያች ታሪክን ባቀፈች፣ ሃይማኖትን በያዘች ከተማ ታደሱ፤ ምሥጋናውን አንሱ፤ በፍቅር እና በሰላም ተመላለሱ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!