
ባሕር ዳር: ጥር 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ እየተሳተፉ ነው። የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በዳቮስ ስዊዘርላንድ መካሄድ ጀምሯል።
ለ54ኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የዘንድሮው ጉባኤ ጭብጥ ” መተማመንን ዳግም መገንባት” የሚል ሲሆን፥ ቁልፍ በኾኑ ዓለም አቀፍ የልማት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ አየር ንብረት ለውጥና ወቅታዊ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
አቶ ደመቀ በጉባኤው ላይ እያደረጉት ካለው ተሳትፎ ጎን ለጎን ከሀገራት መሪዎች እና ከተቋማት ኀላፊዎች ጋርም ውይይት አድርገዋል። ከታንዛኒያ ምክትል ኘሬዚደንት ፊሊኘ ምፓንጎ ጋር በነበራቸው ውይይትም አቶ ደመቀ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስለሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ አብራርተዋል። የኘሮጀክቱ አጠቃላይ ሥራ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልፀውላቸዋል።
የታንዛኒያ ምክትል ኘሬዚደንት ፊሊኘ ምፓንጎ በዓባይ ውሃ ሃብት ላይ ፍትሐዊ አጠቃቀም በተፋሰሱ ሀገሮች መካከል እንዲሰፍን ታንዛኒያ የምታደርገውን ጥረት እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶች በውይይት እንዲቋጩ ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል ። የሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባን በቅርቡ ለማካሄድ ተስማምተዋል።
አቶ ደመቀ ሌላውን ውይይት ያደረጉት ከዓለም አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዳረን ታንግ ጋር ነው። ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ያላት ትብብር ሊጠናከር በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ዝግጁ መኾኗንም ተናግረው ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አቶ ደመቀ ያቀረቡላቸው ጥሪም ተቀብለዋል።
ዋና ዳይሬክተር ዳረን ታንግ የዓለም አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!