
ባሕር ዳር: ጥር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሚሠሩ የውኃ ተቋማት የወደፊቱን የከተሞችን እድገት ታሳቢ ያደረጉ መኾናቸውን በባሕር ዳር ከተማ በቅርቡ አገልግሎት ላይ የዋለውን የውኃ ፕሮጀክት ለጎበኙ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ገለጻ ተደርጓል።
የክልሉን ሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውኃ ጥያቄ ለመመለስ የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጅ ቢሮ ከመንግሥት፣ ከአጋር አካላት እና ከዓለም ባንክ በተገኘ በጀት አዳዲስ እና የማሻሻያ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ የቢሮው ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በተለምዶ “ዓባይ ማዶ” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ለሚኖሩ ከ140 ሺህ በላይ ሕዝብ በ650 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት አንዱ ማሳያ እንደኾነ ተነስቷል።
ፕሮጀክቱ የከተማዋን ግማሽ ሕዝብ የውኃ ችግር ለቀጣይ 25 ዓመታት እንደሚፈታ ኀላፊው ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈ በሃሙሲት በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የንጹህ መጠጥ ውኃ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
በሌሎች ከፍተኛ ውኃ ችግር ባለባቸው እንደ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ ደሴ እና ደብረ ብርሃን በመሳሰሉ ከተሞች የመሥመር ማሻሻያ፣ የጉድጓድ ጠረጋ፣ ተጨማሪ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ማሻሻል ሥራዎች እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በገጠሩ የክልሉ አካባቢዎች የሚነሱ የውኃ ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ያለውን ውኃ በፍትሐዊነት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድርግም እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!