“የክልሉ የሰላም ሁኔታ መሻሻል በማሳየቱ የልማት ሥራዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን

31

ባሕር ዳር: ጥር 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴንን ጨምሮ የክልል ቢሮዎች የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች በከተማ አሥተዳደሩ የተሠሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንን ጎብኝተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን እንዳሉት በክልሉ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ተጠናቅቀው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ሁሉም ለሰላም ሊሠራ ይገባል።

የሰላሙ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል በማሳየቱ በክልሉ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የክልሉን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ መንግሥት ባደረገው የሰላም ጥሪ በሺህ የሚቆጠሩ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ሥልጠና እየወሰዱ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

አሁንም መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በግጭት ዓላማን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ትርፉ ጥፋት መኾኑን ተረድተው ለሰላም እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጥምቀት እና ሌሎች በዓላትን በሰላም ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል። በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ማኅበረሰቡ ሰላሙን በራሱ መጠበቅ ይገባዋልም ብለዋል።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) እንዳሉት መንግሥት ከሕግ ማስከበሩ ባለፈ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየሠራ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ በአዲስ የሚሠራውን የዓባይን ድልድይም በማሳያነት አንስተዋል።

ድልድዩ የባሕር ዳር ከተማን ብቻ ሳይኾን ከመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን የትራንስፖርት መጨናነቅ የሚፈታ ነው። ከዚህም ባለፈ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ በመኾኑ በክልሉ መንግሥት በየጊዜው ክትትል እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችም በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ለሕዝብ የማስተዋወቅ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። ማኅበረሰቡም የሚሠሩ የልማት ሥራዎችን ሊጠብቃቸው ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኮንትራት ቅጥር ማስታወቂያ
Next articleየኮንትራት ቅጥር ማስታወቂያ