
ባሕር ዳር: ጥር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በአማራ ክልል አርሶ አደሮች የሚተገበር የመሬ መልሶ ማገገም አቀጣጣይ ፕሮጀክት እወጃ እና ትውውቅ አድርጓል።
የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በአማራ ክልል ሊተገብረው ያቀደው የተፈጥሮ እንክብካቤ ሥራ ፕሮጀክት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ስለኾነ ሁለንተናዊ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አልማዝ ግዛው (ዶ.ር) አካባቢን መጠበቅ እና ማልማት በግለሰብ እና በአንድ ተቋም ብቻ የሚተገበር አለመኾኑን ጠቁመዋል። የተፈጥሮ ሃብት እና የግብርና ችግሮች እና ልማቶች የሚመጋገቡ ስለኾኑ ተቀናጅቶ በመሥራት ተፈጥሮን መታደግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የኑሮ ማሻሻል እና የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራም ኀላፊ ይድነቃቸው ወንድአፈረው ወርልድ ቪዥን ላለፉት 20 ዓመታት የአካባቢ ማገገም ሥራ ልምድ እንዳለው ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን የማገገም ዕቅድ ያለው ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የዚህ አካል የኾነውን የአማራ ክልል ፕሮግራም አስጀምሯል ነው ያሉት።
ፕሮጀክቱ በተፈጥሮ ሃብት፣ በግብርና እና የዕለት መተዳደሪያ ገቢ በማስገኘት ላይ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ የአካባቢ መራቆት፣ የበረሃማነት መስፋፋት እና የብዝኃ ሕይወት መመናመን የሚፈጥረውን ችግር ለመቀነስ እንደሚያስችል ነው ያስገነዘቡት። የረጅም ጊዜ ውጤት በማስገኘት እና የማኅበረሰብ ችግርን በመቅረፍ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የገለጹት።
በግብርና ሚኒስቴር የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም ከፍተኛ ባለሙያ እና የሚኒስቴሩ ተወካይ ግርማ ክብረት ፕሮጀክቱ የአርሶ አደሮችን አቅም ተጠቅሞ መሬትን መልሶ በማልማቱ፣ በቀላል ወጪ ሰፊ ቦታ መሸፈኑ እና ባሕላዊ ዕውቀትን በመጠቀም አሳታፊነቱ ተመራጭ እንደሚያደርገው አስረድተዋል። በእወጃ እና የአጋር አካላት ትውውቅ ውይይቱ ላይም የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልኾኑ የልማት ድርጅቶች ተወካዮች ተካፍለዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!