
ባሕር ዳር: ጥር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ከባሕር ዳር፣ ከጎንደር፣ ከወሎ፣ ከወልድያ እና ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሥነ ምድር ጥናት እና ካርታ ሥራ እንዲሁም በከፍተኛ መስፈርት የማዕድን ፍለጋ፣ ክምችት፣ ስርጭት እና ጥራት የሚያመላክቱ ጥናቶችን የሰነድ ርክክብ አድርጓል።
የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ታምራት ደምሴ የጥናቱ ዓላማ በክልሉ የሚገኙ ማዕድናት ያሉበትን ቦታ ካርታ የመለየት፣ የማጥናት፣ ዓይነታቸውን ማወቅ እና አዋጭነቱን መተንተን መኾኑን ገልጸዋል። የማዕድናትን ስርጭት አጥንቶ ለአልሚ ባለሃብት ለማቅረብ መታሰቡንም አክለዋል።
“ማዕድን አዲስ የንጋት ተስፋ ለክልላችን” በሚል መርህ በሁሉም የክልላችን ቦታዎች ጥናት ለማድረግ እየሠራን ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው በዚህ ጥናት አምስት ዩኒቨርሲቲዎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ደግሞ የማዕድናቱን ክምችት መጠን እና ተዛማጅ ጉዳዮች እንደሚጠኑ አሳውቀዋል።
እንደ አቶ ታምራት ገለጻ እስካሁን በተጠኑ ጥናቶች የስሚንቶ ምርት ዋነኛ ግብዓት ተገኝቷል። ሥራው ተጠናክሮ ሲቀጥል ወርቅን ወደ ውጪ በመላክ ምንዛሬ ማግኘት እና ከውጪ የሚገቡትን በመተካት ለምጣኔ ሃብት ዕድገት ይጠቅማል።
በተጨማሪም ወጣቶች፣ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን በጌጠኛ ድንጋይ እና ቀለል ባሉ ማዕድናት በማውጣት እንዲጠቀሙም እናደርጋለን ብለዋል። በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድር ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ አበባው ቢተው በ2015 ዓ.ም ባደረግነው ጥናት በሰሜን ወሎ፣ እና በደቡብ ወሎ ዞን ውጫሌ እና በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተለያዩ ማዕድናት መኖራቸውን ለይተናል ብለዋል።
የተለያዩ ውድ ዋጋ ያላቸው ማዕድናት መገኘታቸውን የገለጹት መምህር እና ተመራማሪው የብረት፣ ሊቲየም፣ ግራናይት፣ ሲልክ ሳንድ ከተገኙት ማዕድናት መካከል መኾናቸውን ጠቅሰዋል። በተለይም በዋግ ኽምራ አካባቢ የተገኙ ማዕድናት የተለዩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ዋና ጸሐፊ እና ከአስተባባሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት አስማረ ደጀን (ዶ.ር) የቀድሞ የጥናት ካርታ በአማራ ክልል ማዕድን እንደሌለ ተደርጎ ነበር የተዘጋጀው ብለዋል። ያ ደግሞ የውጪ ባለሃብት እንዳይመጣ እና የኛ ባለሃብቶችም ተስፋ እንዲቆርጡ ያደረገ ነበር ብለዋል።
አሁን ላይ በተደረገው ጥናት በአማራ ክልል የተለያዩ ማዕድናት በሰፊው መኖራቸው ተረጋግጧል ነው ያሉት። ወርቅ፣ ሊቲየም፣ የደንጋይ ከሰል እና ብረት በተለያዩ አካባቢዎች መኖራቸውን በጥናቱ ከተረረጋገጡት ውስጥ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል።
የማዕድናት በሀገር ውስጥ መመረት ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት እና የግብርናውን ምጣኔ ሃብት ለማገዝ ያስችላል ያሉት ዶክተር አስማረ ኢንዱስትሪዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ድህነትን ለመቀነስ ያስችላሉ ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የንድፈ ሃሳብ እውቀታቸውን ወደ ተግባር ለውጠው ለሀገር እንዲጠቅሙ እና ተማሪዎቻቸውን በተግባር በማስተማር የሥነ ምድር ትምህርት ተፈላጊ ዘርፍ ማድረግም ያስችላል ብለዋል።
ርክክብ የተደረገው ሰነድ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች በ15 ወረዳዎች ያደረጉት የማዕድን ጥናት መኾኑን እና በቀጣይም በስፋት እንደሚጠና ገልጸዋል።
ዘጋቢ ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!