
ደሴ: ጥር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የ2016 በጀት ዓመት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ሥር በሚገኘው 011 ቀበሌ ወበሳ ተፋሰስ መጀመሩን የከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
በተፋሰስ ሥራ ላይ ሲሳተፉ ያገኘናቸው አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራው ከዚህ በፊት ጥቅም አይሰጡም ተብለው የነበሩ መሬቶችን በማልማት የአፈር ለምነት መቀነስን ለመከላከል እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ዳንኤል ጌታቸው በ12 የተፋሰስ ቦታዎች ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት በእቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱንም አስረድተዋል፡፡
ኀላፊው ኮምቦልቻ ከተማ የኢንዱስትሪ መንደር እንደመኾኗ የተፈጥሮ ሃብት ሥራን መሥራት የአካባቢ ሥነ ምሕዳርን ከመጠበቅ አኳያ አይተኬ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ የተናገሩት መምሪያ ኀላፊው ከ850 ሺህ በላይ ችግኞች እደሚተከሉም ጠቁመዋል።
በተመረጡ የተፋሰስ ቦታዎች ከ2 ሺህ በላይ ሰዎችን በማሳተፍ ለ25 ቀናት እንደሚከናወንም አብራርተዋል፡፡ ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራው በተጓዳኝ የበጋ መስኖ እና የመኸር ሰብል ልማት ሥራዎችም እንደሚሠሩ ተገልጿል።
ዘጋቢ:-ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!