
ባሕር ዳር: ጥር 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወልድያ ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ቅበላ ጥር ስድስት ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩንም ገልጿል። የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ብርሃን ደጀን እንደገለጹት በክልሉ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም ዩኒቨርሲቲው ከጥር ስድስት ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን መቀበል ጀምሯል።
በክልሉ በነበረው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት በመደበኛው የትምህርት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሂደቱን እንዳልቻለ አስታውሰው፤ አሁን ላይ በአማራ ክልል ያለውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም ዩኒቨርሲቲው ስድስት ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል።
ነባር የሁለተኛና የሶስተኛ ዓመት ተማሪዎች እንዲሁም በ2015 ዓ.ም የአቅም ማሻሻያ ፕሮግራም ትምህርት ተከታትለው የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ወደዩኒቨርሲቲው መግባት መጀመራቸውን ተናግረዋል::
በ2014 ዓ.ም እና በ2015 ዓ.ም በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርት አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎች እና በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው የማለፊያ ውጤት አስመዝግበው በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ለተመደቡ ተማሪዎች እየገቡ መኾኑንም ገልጸዋል።
የተማሪዎች ኅብረትና የተማሪ በጎ አድራጎት ማኅበር አስፈላጊውን ባጅ አዘጋጅተው ተማሪዎችን መናኸሪያ እና በዩኒቨርሲተው መግቢያ በሮች ቅበላ እያደረጉላቸው መኾኑን ገልጸዋል::
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲውና የከተማው የጸጥታ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል። ለረጅም ጊዜ ተዘግተው የቆዩ የተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎች ላይ አስፈላጊው የኬሚካል ርጭት፣ የቀለም ቅብና የማጽዳት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
ተማሪዎች እንደገቡ የመማር ማስተማር ሂደቱን በቀጥታ ለማስጀመር የመማሪያ ክፍሎችን፣ መምህራንን እና አስፈላጊ የቤተ ሙከራ ግብዓቶች ዝግጁ መደረጋቸውን አስታውቀዋል::
ከመማር ማስተማር ግብዓቶች በተጨማሪም የምግብ ግብዓት ተማሪዎች ከመግባታቸው ቀድሞ ዝግጁ መደረጋቸውን አስረድተዋል:: ከጥር ስድስት ቀን እስከ ጥር ሰባት ቀን 2016 ዓ.ም መደበኛ ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል። ጥር ስምንት ደግሞ በቅጣት ምዝገባ ይከናወናል ብለዋል።
አቶ ብርሃን እንደገለጹት፤ ጥር ዘጠኝ አጠቃላይ ገለጻ በመስጠት ከጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል እቅድ ተይዟል።
ኢፕድ እንደዘገበው ተማሪዎች ለአምስት ወር ያህል ከትምህርት ገበታ ርቀው የቆዩ መኾናቸውን አስታውሰው፤ ተማሪዎች አስፈላጊውን ዕውቀት አግኝተው የላቀ ውጤት እንዲያዝመዘግቡና ለመውጫ ፈተና እንዲዘጋጁ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!