“ጥምቀትን በጎንደር በድምቀት ለማክበር በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል” የጎንደር ከተማ አስተዳደር

28

ባሕር ዳር: ጥር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጥምቀት በዓልን በደመቀ ሁኔታ በጎንደር ከተማ እንዲከበር የዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መኾኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ::

የጎንደር ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኀላፊ አበበ ላቀው የጥምቀት በዓልን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በከተማ ደረጃ በከንቲባ የሚመራ አንድ ዐብይ ኮሚቴ እና ስምንት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተደራጅተው ወደ ሥራ ገብተው የዝግጅት ሥራዎችን እያተጠናቀቁ ነው ብለዋል::

በተለይም በጎንደር ፋሲለደስ ባህረ ጥምቀት በሚከናወንበት ሥፍራ የሚያስፈልጉ የጽዳት እና ሌሎች ጊዜያዊ ሥራዎች ተጠናቅቀዋል ብለዋል:: አቶ አበበ በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር አስፈላጊው ውይይት መደረጉን አስታውቀዋል።

በውይይቱ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ከባለፉት ዓመታት በተለየ መንገድ ዝግጁ መኾናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል ያሉት አቶ አበበ “ጥምቀትን በጎንደር በድምቀት ለማክበር በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል” ብለዋል።

በተጨማሪም ከክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በጋራ በተሠራ ሥራም ክብረ በዓሉን በከተማው ለመታደም ለሚመጡ ጎብኚዎች ከላሊበላ በቀጥታ ጎንደር የአየር ትራንስፖርት የተጀመረ መኾኑንም አስታውቀዋል::

እንዲሁም በከተማው የተሟላ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ ሲሆን ከአየር ማረፊያ ሆቴል የሚያደርሱ እና ከተማ ውስጥ ለውስጥ የሚያስጎበኙ በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል::

አቶ አበበ እንደገለጹት በዓሉ የከተማውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት ትልቅ ፋይዳ አለው:: ይህንንም ለመጠቀም ሰላም ዋና መሠረት ያሉት ኀላፊው ሕዝቡ የጸጥታው ባለቤት እንደኾነ በተደጋጋሚ በተዘጋጀ መድረክ ተረጋግጧል ብለዋል::

እንግዶች የጥምቀት በዓልን በከተማው ከማክበር ባለፈ ቆይታቸውን የሚያራዝሙባቸው፣ የአካባቢውን ጸጋ የሚመለከቱበት ብሎም በዘርፉ ላይ ኢንቨስት የሚደርጉበትን ሁኔታዎች መመቻቸቱንም ነው የገለጹት:: ከበዓሉ በፊት የባህል ሳምንት መድረክ የሚዘጋጅ መኾኑን ጠቁመው፤ ሰፊ የማኅበረሰብ ክፍል የሚሳተፍበት በመኾኑ የዝግጅት ሥራዎች እንደተሠሩ አቶ አበበ አስታውቀዋል::

እንዲሁም በዓሉን ምክንያት በማድረግ በበዓሉ ማግስት በከተማ ደረጃ የኢንቨስትመንት ፎረም ይካሄዳል:: በዚህ መድረክም እንግዶችን በኢንቨስትመንት ለማሳተፍ በግልጽ ጨረታ ከ 12 ነጥብ 7 ሄክታር በላይ መሬት በሊዝ ለባለሃብቶች ለማስተላለፍ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል::

በአሁኑ ጊዜ ጎንደር እና አካባቢው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሰፍኗል ያሉት አቶ አበበ በከተማው የተሟላ አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል:: እንግዶች ያለምንም ስጋት በዓሉን ማክበር እና መታደም እንደሚችሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል::

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ቱሪዝም ከአምስቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሰሶዎች አንዱ እንደመኾኑ መጠን የግሉ ዘርፍ ወሳኝ ሚና እንዳለው እንገነዘባለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleወልድያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ መርሐ-ግብር የሚማሩ ተማሪዎቹን እየተቀበለ መኾኑን አስታወቀ።