ከ6 ሺህ በላይ በምገባ መርሐ ግብር መታቀፍ ያለባቸው ተማሪዎች መለየቱን የደሴ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

23

ደሴ: ጥር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደሴ ከተማ አሥተዳደር ከተስፋ ድርጅት ደሴ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር የተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብርን በደሴ ከተማ አስጀምሯል፡፡

የምገባ መርሐ ግብሩ በሮቢት እና በመርሐ ጥበብ ትምህርት ቤት የሚማሩ 2 ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የተስፋ ድርጅት ደሴ ቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጅ ተስፋየ መከተ ተናግረዋል፡፡

የምገባ መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በከተማ አሥተዳደሩ ከ6 ሺህ በላይ በምገባ መርሐ ግብር መታቀፍ ያለባቸው ተማሪዎች ተለይተዋል ብለዋል፡፡

እነዚህ ተማሪዎች በምግብ እጥረት ውስጥ ኾነው እንዳይማሩ ከተማ አሥተዳደሩ የጀመረውን የምገባ እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ ያሉ ሀገር ወዳዶች ሰብዓዊ ተግባሩን እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡

ብቁ እና ተወዳዳሪ የነገ ተስፋዎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ሁሉም እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በቀጣይ ከተማ አሥተዳደሩ ሃብት በመመደብ በሁለት ትምህርት ቤቶች የተጀመረውን የምገባ ፕሮግራም ወደ ሌሎችም ለማስፋት እየተሠራ እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል የማኅበረሰብ ንቅናቄ ለማስጀመር የታሰበውን በጎ ተግባር መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት እንዲሁም ባለሃብቶች እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ጀማል ይማም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሠራተኞች በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይን ጎበኙ።
Next articleበሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።