የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ እንደ ወትሮው ሁሉ እንደሚከበር ብፁዕ አቡነ ዮሃንስ ገለጹ፡፡

146

ጎንደር: ጥር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሃንስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን የእዳ ደብዳቤ በማየ ዮርዳኖስ ለመቅደድ በ30 ዓመቱ የመጠመቁ መታሰቢያ በዓል መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በየዓመቱ ጥር 11ቀን የሚታሰበው የጥምቀት በዓል ሰዎች በክርስትና አምነው የሚጠመቁበት እና ልጅነት የሚያገኙበት እንደኾነ በወንጌል መፃፉንም አንስተዋል።
ከዚህ በመነሳት ወንዶች በተወለዱ በ40 ቀን፣ ሴቶች ደግሞ በተወለዱ በ80 ቀን እየተጠመቁ የቤተክርስቲያን አባል እንዲኾኑ ሕግ የተቀመጠበት፤ የሰው ልጆች ሃጢያት እንዲደመሰስ መንገድ የተከፈተበት በዓል ነው ብለዋል።

ብፁዕ አቡነ ዮሃንስ ጥምቀት በዩኔስኮ የተመዘገበ እና በተለይም በጎንደር ለሚከበረው በዓል የተለያዩ እንግዶች ከበርካታ የዓለም ክፍል እንደሚመጡ ገልጸው በዓሉን በሰላም ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ብፁዕነታቸው በሰጡት ማሳሰቢያ በዓላት በተለያየ መልክ እንደሚከበሩ አንስተው በአደባባይ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ እንደ ወትሮው ሁሉ እንደሚከበርም አንስተዋል።
የጥምቀት በዓል ይከበራል አይከበርም የሚለው ውዥንብር ተገቢነት የለውም ያሉት ብፁዕነታቸው በቀኖና ቤተክርስቲያን መሰረት ጥምቀት ይከበራል ብለዋል።

ጥምቀት በሚከበርበት ሰዓት ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡትን በተለይም የፀጥታ አካላትን እና ወጣቶችን ማገዝ እና መተባበር እንደሚገባ አንስተዋል።

ጥምቀት አይከበርም ብሎ መከልከል ሃይማኖታችሁን እና ማተባችሁን በጥሱ እንደማለት ነው ያሉት ብፁዕነታቸው በጎንደር ከተማ የሚከበረው ጥምቀት እንደ ወትሮው ሁሉ የሚከበር በመኾኑ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲጫወት አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኮንትራት ቅጥር ማስታወቂያ
Next articleየኮንትራት ቅጥር ማስታወቂያ