በባሕር ዳር ከተማ የተሠሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ለሕዝብ ክፍት እንደሚኾኑ የከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ።

31

ባሕር ዳር: ጥር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማን የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስፋፋት የተሠሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ለሕዝብ ክፍት እንደሚኾኑ የከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ገልጿል።

“ጥርን በባሕር ዳር” በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው። በከተማ አሥተዳደሩ የተገነቡ የአረንጓዴ ልማት ቦታዎችን ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጉብኝት አድርገዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው እንዳሉት የባሕር ዳር ከተማን የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስፋት ከተማ አሥተዳደሩ ከተማዋን የማስዋብ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል።

የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የቲያትር ቤት፣ የስፖርት ቤቶች፣ የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት፣ የአባት አርበኞች ገድሎች እና ከጤና ቱሪዝም ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ጭምር ያካተተ ነው።

የአረንጓዴ ልማት ሥራዎቹ ለበርካታ ወጣቶችም የሥራ እድል የመፍጠር አቅም ያላቸው መኾኑን ገልጸዋል። የልማት ሥራዎቹ የከተማዋ ምጣኔ ሃብት እንዲነቃቃ እድል ይፈጥራል ብለዋል። የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜም እንደሚያራዝም ጠቅሰዋል።

ጥርን በባሕር ዳር ለማክበር አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተለይም ደግሞ ሆቴሎች ዝግጁ እንዲኾኑ ተደርጓል ብለዋል። በዓሉ የሕዝብ በዓል በመኾኑ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

በከተማዋ የተሠሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የቱሪዝሙን ዘርፍ ይበልጥ እንዲነቃቃ አቅም እንደሚፈጥሩ ጎብኝዎች ገልጸዋል። የተሰሩት የልማት ሥራዎች ወጣቶች ከአልባሌ ቦታ ወጥተው ራሳቸውን በሚጠብቁበት ቦታ ላይ እንዲያዘወትሩ ያደርጋል።

በቀጣይም የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስፋት እና ተጨማሪ የሥራ እድል ለመፍጠር የጣና ሐይቅ ደኅንነት በጠበቀ መንገድ የሐይቁን ዳርቻዎች ማልማት ያስፈልጋል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአፄ ቴዎድሮስ 205ኛው የልደት ቀን በጎንደር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ።
Next articleየኮንትራት ቅጥር ማስታወቂያ