
ባሕር ዳር፡ ጥር 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአፄ ቴዎድሮስ የልደት በዓል ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ ፤ በዘመነ መሳፍንት ሀገር ተከፋፍሎ ሲባላ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያን ትንሳኤ ያበሰረ የአንድነት መነሻ ዋልታና ማገር የሆነ መሪ እንደነበረ ገልጸዋል።
አፄ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያ አንድነት የሚመጣው በሳይንስ፣ በምርምርና በኪነጥበብ ነው ብለው የሚያምኑ ንጉስ ናቸው ያሉት ወይዘሮ ደብሬ፤ ሁላችንም አባቶቻችን ሰርተው የሰጡን ሀገር በጋራ በመፈቃቀር ወንድማማችነትና እህታማማችነትን በማፅናት የአባቶቻችንን ታሪክ በመድገም የአካባቢያችንን እንዲሁም የሀገራችንን አንድነት ልናፀና ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ዮናስ ይትባረክ በበኩላቸው አፄ ቴዎድሮስ በዘመነ መሳፍንት ተከፋፍላ የነበረችውን ኢትዮጵያ ወደ አንድ በማምጣት ትልቅ ታሪክ የሰሩ ናቸው ። 205ኛውን የልደት በዓላቸውን ስናከብር ትውልዱ ለሀገራችን አንድነትና አብሮነት ሊማርበት እንደሚገባ አቶ ዮናስ ተናግረዋል ። የልደት በዓሉን አስመልከቶ በአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ የአበበ ጉንጉን ተቀምጧል ።
በጎንደር ከተማ ከዛሬ ጀምሮ የጥምቀት የበዓል ሳምንት በተለያዩ ኩነቶች በድምቀት እንደሚከበር ጠቁመዋል ። መረጃው የጎንደር ከተማ ኮሙኒኬሽን ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!