ለስጋ ደዌ በሽታ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ማጥፋት እንደሚገባ የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበረዊ ጉዳይ ቢሮ አሳሰበ።

10

ባሕር ዳር: ጥር 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከጤና ቢሮ እና ከአማራ ክልል ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኅበር ጋር በመተባበር የስጋ ደዌ ቀንን አክብሯል። ቀኑ በዓለም ለ70ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ25ኛ ጊዜ “ስጋ ደዌን አንዘንጋ” በሚል መሪ መልእክት ነው የታሰበው።

ስጋ ደዌ ለዓመታት በእርግማን የሚደርስ የማይድን ሕመም ተደርጎ ይወሰድ እንደነበር ተመላክቷል። ይህ አስተሳሰብ ዛሬም ቢኾን ጨርሶ አልጠፋም። ለዘመናት በቆዬው የተሳሳተ አመለካከት የስጋ ደዌ ተጠቂዎች በመገለላቸው ለተለያዩ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቡናዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ለሰበዓዊ መብት ጥሰቶች ሲዳርግ መቆየቱም ተመላክቷል። የቆዬው የተሳሳተ አመለካከት የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ታክመው ወደ ማኅበረሰቡ ለመቀላቀል ይቸገሩ እንደነበር ተነስቷል።

ስጋ ደዌ እንደማንኛውም በሽታ በሕክምና የሚድን ነው። በተለይም የጣምራ መድኃኒት ከተገኘ ጀምሮ ስጋ ደዌን ማዳን እንደሚቻል ነው የተገለጸው። የስጋ ደዌ ተጠቂዎች የእኩል እድል እና ሙሉ ተሳትፎ ተጠቃሚዎች እንዲኾኑ ማድረግ፣ እንደሌሎቹ ሁሉ መታከም እንዲችሉ ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል።

የአማራ ክልል ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኅበር መሥራች እና አባል የሽመቤት ካሴ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች በስጋት ራሳቸውን ያገላሉ፣ ማኅበረሰቡም ያገላል ነው ያሉት። አመለካከትን በማስተካከል መኖር ይቻላል ብለዋል። እሳቸውም ራሳቸውን ሳይደብቁ መኖራቸውን እና ታክመው መዳናቸውን አንስተዋል። ራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩ ወገኖች መውጣት እና በሕክምና መዳን እንደሚችሉም ገልጸዋል። በስጋ ደዌ መጠቃት ዝቅ ማለት አለመኾኑንም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኅበር ጸሐፊ ይመር በየነ በነበረው የተሳሰተ አመለካከት የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ራሳቸውን ደብቀው ለችግር ሲጋለጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ሲገለሉ እና ሲርቁ መቆየታቸውን ነው ያነሱት። የስጋ ደዌን በሕክምና ማዳን ይቻላል፣ ባለማወቅ ግን ተደብቀው ይኖራሉ ነው ያሉት።

እሳቸው የስጋ ደዌ ተጠቂ በኾኑበት ጊዜ መጠቋቆሚያ ይኾኑ እንደነበርም አስታውሰዋል። ተጠቂዎችም ወደ ሕክምና ሄደው መታከም አለባቸው፣ ማኅበረሰቡም አመለካከቱን ማስተካከል ይገባዋል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ መጠቋቆሚያ ሲያደርግ ከበሽታው በላይ ሌላ ችግር ይመጣል ብለዋል።

የአማራ ክልል ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኅበር ሊቀመንበር ምንይችል ደምለው የስጋ ደዌ በሽታ በርካታ ወገኖችን ሲቀጥፍ እንደቆዬ አስታውሰዋል። በጤና ሚኒስቴር እና በጤና ቢሮ በተሠራው ሥራ አሁን ላይ መቀነስ እንደታየበትም ገልጸዋል። አሁንም ሁሉም ለስጋ ደዌ ትኩረት በመስጠት መከላከል ይገባዋል ነው ያሉት። በስጋ ደዌ የተጠቁ ወገኖች በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዳይገለሉ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

“አትቅረቡን ይተላለፍብናል እየተባልን ስንገለል ኖረናል” ያሉት ሊቀመንበሩ አሁንም ይህ አስተሳሰብ ባለመቀየሩ ሊስተካከል ይገባል ነው ያሉት። ማኅበሩ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚ እንዲኾኑ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የስጋ ደዌ፣ ቲቢ እና ኤች አይቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክተር ገብሬ ንጉሤ የስጋ ደዌ ተጠቂ የኾነ ሰው በፍጥነት ወደ ሕክምና ካልሄደ ለአካል ጉዳት ይዳረጋል ነው ያሉት። በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው መገለል ተጎጂዎች እንዲደበቁ እንደሚያደርጋቸውም አንስተዋል። የስጋ ደዌ በሽታ ሕክምና በነፃ እንደሚሰጥም አመላክተዋል። ምልክቱ ያለባቸው ወገኖች ወደ ጤና ተቋማት እየሄዱ መታከም እንደሚችሉም ገልጸዋል።

የስጋ ደዌ በሽታ በዘር ወይም በእርግማን የሚመጣ አለመኾኑንም ያነሱት ዳይሬክተሩ በዘር እና በእርግማን እንደሚመጣ አድርጎ ማሰብ የተሳሰተ መኾኑንም ተናግረዋል። እንደማንኛውም በሽታ በተህዋስያን የሚመጣ እና በሕክምና የሚድን መኾኑንም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንፁሕ ሽፈራው ተጠቂዎች የነበሩበትን አሰቃቂ ሁኔታ እና የሰበዓዊ ጥሰት ለመከላከል በማሰብ በዓሉ መከበር መጀመሩን ነው የተናገሩት። በዓሉ የሚከበረው ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማረም መኾኑንም አንስተዋል።

የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ጥያቄ ዘርፈ ብዙ በመኾኑ ምላሹም ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል። ቢሮው ስጋ ደዌ ተጠቂዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። ለመብቶቻቸው እንዲደራጁ ማኅበራት እንዲቋቋሙ እና የስጋ ደዌ ተጠቂዎች አባል እንዲኾኑ ማድረጉንም ገልጸዋል። የስጋ ደዌ በሽታ እየተዘነጋ መኾኑን ያነሱት ምክትል ኀላፊዋ በሽታውን መዘንጋት ተጠቂዎችን ለበለጠ ችግር እንደሚያጋልጥም ገልጸዋል።

ለስጋ ደዌ በሽታ ሁሉም አካል ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ማጥፋት እንደሚገባም ምክትል ኀላፊዋ አሳስበዋል። በዓሉን በማክበር ብቻ መከላከል አይቻልም ያሉት ምክትል ኀላፊዋ ሁልጊዜም በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል። ለስጋ ደዌ ያለውን አመለካከት ማስተካከል እና መከላከል እንደሚገባም አመላክተዋል። በሽታውን በጋራ እና በመተባበር ማጥፋት ይገባልም ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእስከ ጥር 17 የሚቆየው የአፍሪካ ኅብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ ተጀመረ።
Next articleየአፄ ቴዎድሮስ 205ኛው የልደት ቀን በጎንደር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ።