
ሰቆጣ: ጥር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መንግሥት በክልሉ የተፈጠረውን የሰለም መደፍረስ ችግር ለመፍታት የሰላም አማራጮችን ቀዳሚ ምርጫ ማድረጉን ሊቀጥል ይገባል ሲሉ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የዝቋላ ወረዳ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የተጀመሩ የሰላም ስምምነቶች የዋግን ሕዝብ ተጠቃሚ ስለማድረጋቸው የዝቋላ ወረዳ ጽጽቃ ከተማ ነዋሪ አቶ አሰፋ ጉለሽ ለአሚኮ ተናግረዋል። ወይዘሮ ሽኳሬ ቸኮለ በበኩላቸው ጦርነት የሀገርን ኢኮኖሚ ከማድቀቁም በላይ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የከፋ ነው ብለዋል።
የዝቋላ ወረዳ አሥተዳደር እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ሃምሳ አለቃ አየነው ተበጀ ችግሮች ሁሉ የሚፈቱት በውይይት እንጅ በአፈሙዝ አይደለም ነው ያሉት። የወረዳው ሕዝብ ከሰላም አማራጮች ጎን በመቆሙ አንጻራዊ ሰላም እንደተገኘ ሁሉ ሌላው አካባቢም የሰላም ምርጫዎችን ሊጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የዝቋላ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ታፈረ ሚሰነ የአማራ ሕዝብ አስተዋይ፣ አርቆ የሚመለከት እና እሴቱን አክባሪ ነው ብለዋል። እንደ ሀገር ከገባንበት የሰላም እጦት የምንወጣው በውይይት ብቻ እንደኾነም አብራርተዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው የዝቋላ ሕዝብ ከሰላም ጎን በመቆም የተገኙትን የሰላም ውጤቶች ለማስቀጠል ሊሠራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!