
ጎንደር: ጥር 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አመራሮችንና አባላትን አቅም ለመገንባትና የተጠናከረ ሕዝባዊ አገልግሎትን ለማጠናከር የሚያስችል የስልጠና መድረክ በጎንደር ማካሔድ ጀምሯል። በሥልጠና ማሥጀመሪያውም የጎንደር ከተማ አሥተዳድር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ስልጠናው በአመለካከት የተስተካከለ የፀጥታ መዋቅር በመፍጠር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል። በወርሐ ጥር የምትደምቀውና ከተለያየ የዓለም ክፍል እንግዶች የሚጎርፉባት፤ ጥምቀትን በድምቀት የምታከብረው ጎንደር ከተማ በፀጥታ ችግሩ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ተጎድቶ መቆየቱን ገልጸዋል። ይህን በመቀልበስ ረገድ የፀጥታ መዋቅሩ ጉልህ ሚና መጫወቱን አንስተዋል። በስልጠናውም የተሻለ አቅም በመፍጠር ወደ ተሟላና ዘላቂ የሰላም እንቅስቃሴ ለመፍጠር መድረኩ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስገንዝበዋል።
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥና የቀጣናው የኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠርና ሕዝቡ ወደ መደበኛ ሥራው እንዲመለስም የተጀመረው ስልጠና ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
የፀጥታ መዋቅሩ ለማንኛውም የፖለቲካ ሀሳብ ውግንና ሳይኖረው በሙያዊ መርህ ላይ የተመሠረተ፤ በግልጽነት ለተልዕኮ የሚያበቃ ስልጠና መሆኑን አንስተዋል። ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በአስተሳሰብም በተግባርም የበቃ የፀጥታ ኀይል በፍጥነት ገንብቶ ሕዝቡ የሰላም አየር እንዲተነፍስ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
በመድረኩ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የርእሰ መሥተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ ይርጋ ሲሳይ “የስልጠናው ተሳታፊዎች ለአንድ አፍታ ሸብረክ ሳንል በልማት ለማበልጸግ ታሪክ፣ባህልና እሴት ያላትን የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ የሆነችውን ሀገር ሌት ከቀን በመሥራት ማገልገል ይገባል” ብለዋል።
ከሁሉም በፊት ኢትዮጵያን የሚያስቀድመው በአብሮነት የቆመው እና አሁንም የክልሉን ሕዝብ ክብር ለማስጠበቅ የሚታገለው የፀጥታ ኀይል ክብር ይገባዋል ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ ፀጥታ ኀይል የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ከመከላከል ወደ መቀልበስ መድረሳቸውንም አቶ ይርጋ ሲሳይ ገልጸዋል።
በቀጣይ በእውቀት፣ ባልተዛነፈ አስተሳሰብ የሚመራ ኀይል በማደራጀት በኩል የተጀመረው ስልጠና ሚናው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።
የእድገት ተስፋ ያላትን ሀገር ጉዞ ማሳካት የሚቻለው በአንድነት የመሪነትን ሚና በተላበሰ መልኩ መሥራት ሲቻል ነው ብለዋል።
የተዛቡ አመለካከቶችንና አስተሳሰቦችን በማረም የፀጥታ መዋቅሩን በማደራጀት፣ በማብቃትና አቅምን ከፍ በማድረግ ተከታታይ ሥራ የሚሠራበት ስልጠና እንዲጀመር መደረጉንም አስታውቀዋል።
የስልጠናውን ፋይዳ ግቡን እንዲመታ ስልጠናው በጥብቅ ዲስፕሊን የሚመራ መሆኑን የገለጹት አቶ ይርጋ ከዚህ ቀደም ያለውን ጥበብና ብልሃት በመጠቀም በሀገር ላይ የተጋረጡ ችግሮችን እንሻገራለን ብለዋል። ስልጠናው ትክክል ያልሆነውን አስተሳሰብ ለማረምና አቅም ለመፍጠር መዘጋጀቱን አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:–ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!