
ባሕር ዳር: ጥር 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ቀጥሎ ሲውል ግብጽ ከሞዛምቢክ፣ናይጄሪያ ከኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጋና ከኬፕ ቨርዴ ይጫወታሉ፡፡
በምድብ ሁለት የተደለደሉት ግብጽ እና ሞዛምቢክ አቢጃን ከተማ በሚገኘው ስታድ ፊሊክስ ሁፉዌት ቦይኒ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ግብጽ በፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት ከአፍሪካ ሀገራት አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የግብጽ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ሰባት ጊዜ አሸናፊ በመኾን ደማቅ ታሪክ ጽፏል፡፡ ፈርኦኖች የአፍሪካ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ የወሰዱት በ1957 ኢትዮጵያን 4 ለ 0 በማሸነፍ መኾኑ ይታወሳል፡፡
ግብጽ ባለፉት 19 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች የተሸነፈችው በአንዱ ብቻ ነው፡፡ በ14ቱ አሸንፋ፣ በአራቱ አቻ ተለያይታለች፡፡ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2021 በናይጄሪያ 1ለ 0 ተሸንፋለች፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ሲታወስ የግብጽ ስኬታማነት ይጠቀሳል፡፡ አምስት ጊዜ ዋንጫውን ያስተናገደች ሀገር ናትና፡፡ በሀገሯ ከተዘጋጀው በሦስቱ [በ1959፣ 1986 እና 2006] አሸናፊ በመኾን አጠናቅቃለች።
የአፍሪካ ዋንጫ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ግብጽ በ26ቱ በመጫወት የላቀ የተሳትፎ ታሪክም አላት፡፡
ቡድኑ በሙሐመድ ሳላህ ፊት አውራሪነት ይመራል፡፡ ሳላህ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 በውድድሩ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰላፊ ከኾነበት ጊዜ አንስቶ ግብፅ ላስቆጠረችው ግብ 64 በመቶው የሳላህ ድርሻ ነው፡፡
ውጤትን አስቀድሞ የሚገምተው ኦፕታ ሱፐር ኮምፒውተር በ2023 የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታ ግብፅ 62 ነጥብ 4 በመቶ እንደምታሸንፍ አስፍሯል፡፡ በግብጽ ብሔራዊ ቡድን በኩል የአል አህሊው አማካኝ አሕመድ ናቢል እና የፒራሚዱን ተከላካይ ኦሳማ ጋላል በጉዳት አይሰለፉም፡፡
የግብጽ ተጋጣሚ የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ አምስተኛው የተሳትፎ ጨዋታው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ባደረጉት የአራት ጊዜ ጨዋታ ከምድባቸው መጨረሻ እየኾኑ ነው ያጠናቀቁት፤ ስለዚህ ለግብጽ ብሔራዊ ቡድን ፈተና ትኾናለች ተብሎ አይጠበቅም እንደ ቢቢሲ ስፖርት ዘገባ፡፡
“እባቦቹ” የሞዛምቢክ ቡድን ቅጽል ስም ነው። ካደረጓቸው 12 ጨዋታዎች ውስጥ ማሸነፍ የቻሉት በአንዱ ብቻ ነው። ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ከሚሳተፉት 24 ሀገራት ውስጥ በ26ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁንና ተናዳፊ እባቦች(ማምባዎች) ሴኔጋል፣ ቤኒን እና ሩዋንዳ ከሚገኙበት የምድብ ማጣሪያ በሁለተኛነት ሊጠናቅቀው ነው ለዚህ ውድድር የበቁት፡፡ ቡድኑ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ባደረጋቸው የወዳጅነት እና የአቅም ማጠናከሪያ ጨዋታዎች ራሱን ፈትሿል። ለአብነትም ሌሴቶን 2 ለ 0 አሸንፏል፡፡ ከቦትስዋና ጋር ደግሞ 1ለ1 ተለያይቷል፡፡ ቡድኑ ካደረጋቸው ሁለት የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች አንዱን አሸንፎ እና በአንዱ መሸነፉ ጥንካሬውን ያሳያል የሚሉም አሉ፡፡
የናይጄሪያው ንስሮቹ አቢጃን ከተማ በሚገኘው እና 60 ሺህ ተመልካች ማስተናገድ በሚችለው የአላሳን ኦውታራ ስታዲየም ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር ይጫወታሉ፡፡ ናይጀሪያ በፊፋ ወቅታዊ የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት 42ኛ ላይ ትገኛለች፡፡
የሀገሪቱ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫን ሦስት ጊዜ ማሸነፍ ችሏል፡፡ ቡድኑም በቪክቶር ኦሲሜን እንደሚመራ አሠልጣኝ ጆሴ ፔሴይሮ ይፋ አድርገዋል።
ንስሮቹ በቅርቡ ከጊኒ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርገው ባልተጠበቀ ሁኔታ 2 ለ 0 በኾነ ውጤት ተሸንፈዋል። ይህም ደጋፊዎችን አስቆጥቷል፡፡
ይህን ተከትሎ የናይጀሪያው አሠልጣኝ ጆሴ ፔሴይሮ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “በተጫዋቾቼ ብቃት አምናለሁ፤ ከግብ ጠባቂው እስከ አጥቂው ድረስ ምዕሉ ነን፤ ጨዋታዎችን በሙሉ እያሸነፍን ዋንጫ እንደምንወስድ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ” ማለታቸውን ኤኤፍፒ አስታውሷል፡፡
ናይጀሪያ የባየር ሊቨርኩሰኑ ቪክቶር ቦኒፌስ፣ የሪያል ሶሲዳዱ ኡመር ሳዲቅ እና የሌስተር ሲቲው ዊልፍሬድ ንዲዲ በጨዋታው አይሰለፉም ተብሏል፡፡ ያም ኾኖ በጨዋታው ናይጀሪያ በከፍተኛ የአውሮፓ ቡድኖች ውስጥ የሚጫወቱ ከዋከብት የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ስላካተተች ታሸንፋለች የሚሉት ወገኖች ላቅ ያሉ መኾናቸውን ዴይሊሜይል አስነብቧል፡፡
የኢኳቶሪያል ጊኒ ብሔራዊ ቡድን በፊፋ ወቅታዊ የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት 88ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡
ኢኳቶሪያል ጊኒ በምድብ ድልድል ምድቧን ከቱኒዚያ ጋር በማጠናቀቅ ነው ለዚህ የደረሰችው፡፡ በምድብ ጨዋታዋ የተሸነፈችው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው፡፡ ይህም ጥንካሬዋን ያሳያል፡፡
ኢኳቶሪያል ጊኒ ከዚህ ቀደም ባደረገቻቸው አስር ጨዋታዎች 6ቱን ስታሸንፍ በአራት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፋለች።
ጋና ከኬፕ ቨርዴም ዛሬ ይጫወታሉ፡፡ የጋና ብሔራዊ ቡድን በፊፋ ወቅታዊ የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት 61ኛላይ ተቀምጧል፡፡ የአራት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዎች ጋና (ጥቋቁር ኮከቦች) እና ኬፕ ቨርዴ በአምስት ጨዋታዎች ተገናኝተዋል፡፡ በአራቱም ጋና ድል ነስታለች፡፡ ኬፕ ቨርዴ መርታት የቻለችው ግንቦት 2021 በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው፡፡
ጋና አራት ጊዜ አህጉራዊው ዋንጫ ብትወስድም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን አቋሟ እንደ ወረደ ስፖርቲ ትራዴር ዘግቧል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚኾነው ጥቋቁር ኮከቦች ከ1982 ጀምሮ ዋንጫ ማንሳት አልቻሉምና ነው ።
ጋና በጉዳት ምክንያት የአርሰናሉን አማካኝ ቶማስ ፓርቴን እና የብራይተኑን ተከላካይ ታሪቅ ላምፕቴን አታሰልፍም፡፡የዌስትሃም ዩናይትዱ መሐመድ ኩዱስን እንዲሁ፡፡
የኬፕ ቬርዴ ብሔራዊ ቡድን በፊፋ ወቅታዊ የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት 73ኛላይ ተቀምጧል፡፡ ብሉ ሻርኮች መጠሪያ ስማቸው ነው፡፡ ሀገሪቱ በአፍሪካ ዋንጫ ለሁለተኛ ጊዜ የሚሳተፉበት ውድድር ነው፡፡ ኬፕ ቨርዴ በምድብ የማጣሪያ ጨዋታ ጠንካራ ተፎካካሪ ኾና ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ነው ያጠናቀቀችው፡፡
የኬፕ ቨርዴ አሠልጣኝ ቡቢ ስታ “ጨዋታውን በጥንቃቄ በመጫወት ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል” ብለዋል። 4-3-3 አሰላለፍንም እንደሚከተሉ ገልጸዋል፡፡ ይንን ጨዋታ ጋና ታሸንፋለች ሲሉ አፍሪክ-ፎት፣ ስኮርስ24፣ ኦፕታ አናሊስት በድረ ገጻቸው ጽፈዋል፡፡
በሙሉጌታ መጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!