
ባሕር ዳር: ጥር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህም ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሀገራዊ ምክክሩ ሂደቶችን ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑ ጠቁመዋል።
ነፍጥ ያነሱ ወገኖች በሰላማዊ መንገድ ወደ ምክክሩ እንዲመጡ መንግሥት ለሰላማዊ አማራጭ ቅድሚያ ሰጥቶ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። ቀደም ብሎ የምክክር ኮሚሽኑን በተመለከተ በሩቅ ኾነው ቅሬታ ሲያነሱ የነበሩ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ላይ የኮሚሽኑን ትክክለኛ ተልዕኮ በቅርበት በመረዳት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት በጋራ ለመሥራት መግባባት ስለመፍጠራቸውም አንስተዋል።
ለአብነትም በቅርቡ ከአፋር ሕዝቦች ፓርቲ፣ ከሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ እና ከኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ማዕቀፍ መፈረሙንም ጠቅሰዋል። ኮሚሽኑ እንደ ገለልተኛ ተቋም ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መሥራት እንደሚፈልግ ገልጸው ሁሉም ፓርቲዎች ወደ ምክክር እንዲመጡ መንግሥት ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክር ሂደት የሚሳተፉበት ዕድል መመቻቸቱንም ገልጸዋል። እስካሁን በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በፓሲፊክ እና እስያ እንዲሁም በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በበይነ መረብ ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል። ከሰሞኑም በአሜሪካ ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይቱ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!