“3ኛዋ የዲፕሎማሲ ከተማ ለኾነችው አዲስ አበባ ተጨማሪ የቱሪዝም አቅም የሚኾኑ ሆቴሎች ያስፈልጉናል” ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ

39

አዲስ አበባ: ጥር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ የተገነባው ባለአራት ኮከብ ሆቴል በአዲስ አበባ ተመርቋል።

የአቶ ተካ አስፋው እና ባለቤታቸው ወይዘሮ ፍቅረማርያም በላይ ድርጅት የኾነው ታፍቢቢ ያስገነባው ደብል ትሪ ባይ ሂልተን የተሰኘው ዓለማቀፍ ሆቴል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል። ሆቴሉ የተጀመረው ከ12 ዓመት በፊት ቢኾንም በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት፣ በፋይናንስ ውስንነት፣ በተደጋጋሚ የዲዛይን ለውጥ፣ በኮቪድ ወረርሽኝ ክስተት እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ቢዘገይም ለምርቃት በቅቷል ያሉት ባለቤቱ አቶ ተካ አስፋው ናቸው። ሆቴሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ600 በላይ ሆቴሎች ያሉት ደብል ትሪ ባይ ሂልተን የተሰኘ ዓለም አቀፍ ብራንድ ሥም መውሰዱን አቶ ተካ ተናግረዋል።

በ75 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተጀመረው ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 650 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎበታል ብለዋል። 300 ለሚኾኑ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አቶ ተካ ገልጸዋል። ሆቴሉን መርቀው የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ከቦሌ አየር መንገድ በቅርብ ርቀት የተገነባው ሆቴሉ የቱሪስት ቆይታን ለማራዘም የሚያስችል ዓለማ አቀፍ ብራንድ ያለው የቱሪዝም ሃብት ነው ብለዋል።

በከተማዋ በግሉ ዘርፍ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ሊበረታቱ ይገባል ያሉት ምክትል ከንቲባው “3ኛዋ የዲፕሎማሲ ከተማ አዲስ አበባ በጤና ቱሪዝም፣ በሆቴል ቱሪዝም እና በሌሎች ኢንደስትሪዎች ማዕከል ለመኾን በምታደርገው ጥረት የግሉ ዘርፍ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንደግፋለን” ነው ያሉት። በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ባለሃብቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶችም ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሴቶች ኅብረ-ብሔራዊነት እንዲጠናከር ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተገለጸ።
Next article“ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ነው” ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ