
ባሕር ዳር: ጥር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሴቶች አሠባሣቢ ትርክት እንዲገነባ እና ኅብረ-ብሔራዊነት እንዲጠናከር ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ብልጽግና ፓርቲ አስታውቋል። የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ የ2016 ዓ.ም 2ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው።
የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መለስ ዓለሙ እንደገለጹት የሴቶች ሊግ በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ብሔራዊነትን በማጉላት የገዥ ትርክት አመለካከት ለመገንባት መሠራት አለበት። ገዥ ትርክት ወይም ብሔራዊነት የኢትዮጵያን ብዝኃነት መቀበል መኾኑን ያስረዱት ኀላፊው ለዚህም የጋራ አቋም በመያዝ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ሊጉ የኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ላይ አመራሩ የድርሻውን እንዲወጣ ለማስቻል መሥራት እንደሚገባው ተናግረዋል። የተናጠል ትርክትን ለማስተካከል የማኅበረሰብ ግንዛቤን የመቀየር ሥራ መሥራት ይገባልም ብለዋል። በሀገሪቱ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሰላም አማራጮች ተግባራዊ እየተደረጉ መኾኑንም አንስተዋል።ችግሮችን ለማቃለል እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ነው ያሉት።
በተለይም ሴቶች ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸውን መስተጋብር ለበጎ ተግባር እንዲያውሉትም ጠይቀዋል። የሊጉ አባላት ባሉበት አካባቢ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ከሚሠሩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው። የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!