“የኢትዮጵያን ሰላም እና ልማት የማይፈልጉ ኃይሎችን እኩይ ዓላማ ለማክሸፍ ሠራዊቱ ዝግጁነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል” ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ

66

ባሕር ዳር: ጥር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያን ሰላም እና ልማት የማይፈልጉ ኃይሎችን እኩይ ዓላማ ለማክሸፍ ሠራዊቱ ዝግጁነቱን አጠናክሮ መቀጠሉን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪ እና የተኩስ አመራር ኀላፊ ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ ገልጸዋል፡፡ የመከላከያ አዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ ለ9ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖች አስመርቋል።

በምረቃ ዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከውስጥም ኾነ ከውጭ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመከላከል የሠራዊቱን የውጊያ ዝግጁነት የማረጋገጥ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አስረድተዋል። ተመራቂዎች በሚመደቡባቸው ቦታዎች ባገኙት እውቀት እና ባላቸው ልምድ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንዲሠሩም አሳስበዋል።

የኮሌጁ አዛዥ ብርጋዴየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው በበኩላቸው በሥልጠናው ያሳለፍናቸውን የውጊያ ልምዶች በመቀመር እና ዓለም የደረሰበትን የወታደራዊ ሳይንስ ጥበብ እና ቴክኖሎጂ በማቀናጀት ለማሠልጠን እንደተቻለ ገልጸዋል። በዝግጅቱ ላይ ከፍተኛ የሠራዊቱ እና የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በምረቃ ማጠናቀቂያው ኮሌጁ እያከናወናቸው የሚገኙ የመሠረተ ልማት ግንባታ እና የፎቶ አውደ ርእይ ለእይታ መብቃቱን ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓመታዊ የአምባሳደሮች ስብሰባ መካሄድ ጀመረ።
Next articleሴቶች ኅብረ-ብሔራዊነት እንዲጠናከር ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተገለጸ።