ቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ ብሔራዊ የጥራት ማረጋገጥ ፕሮግራም ሊተገበር ነው፡፡

26

ባሕር ዳር: ጥር 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ በቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ ብሔራዊ የአገልግሎት ጥራት ማረጋገጥ ፕሮግራም በቅርቡ እንደሚተገበር የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ በቱሪዝም ዘርፍ የአገልግሎት ጥራት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት አንስተዋል።
ጎብኝዎችን በሚያስተናግዱ እንደ ሆቴል እና መሰል ተቋማት ጥራት እንዳይኖር ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል አለመገንባት፣ የሥልጠና እና የልህቀት ተቋማት ማነስን ለማሳያ ጠቅሰዋል።

ችግሩን ለመፍታትም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ የማድረግ እና ደረጃውን የጠበቀ ወጥ አሠራር የመፍጠር እና የልህቀት ማዕከል ለመገንባት እየተሠራ ነው ብለዋል።

አስጎብኝ ድርጅቶችን ጨምሮ ለቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የብቃት ማረጋገጥ ሥራ እየተተገበረ መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህም ባለኮከብ ሆቴሎች የሚሰጡት የአገልግሎት ጥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ አቻ ሆቴሎች ተመሳሳይ መኾን እንደሚገባውም ተናግረዋል።

የአገልግሎት ጥራትን በሁሉም አካባቢ ወጥነት ባለው መልኩ ለማሻሻልም ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላ ብሔራዊ የአገልግሎት ጥራት ማረጋገጥ ፕሮግራም በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ይህም የአገልግሎት ጥራትን ከማስጠበቅ ባሻገር የጥራት መጓደልን የሚጠየፍ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ገልጸዋል። ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ ከ40 ዓመታት በኋላ በአንድ ጊዜ ሦስት ቅርሶችን በመንግሥታቱ ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ማስመዝገቧ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

ይህም ለሀገር ገጽታ ግንባታ፣ የመስህብ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ እና ለማልማት እንዲሁም ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መኾኑን አንስተዋል። ዩኔስኮ ዕውቅና ለሰጣቸውም ኾነ ገና ላልተመዘገቡ ቅርሶች ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የግሉ ዘርፍ እና ማኅበረሰቡ ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር ከመንግሥት ጋር በቅንጅት እንዲሠራ ጠይቀዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው በቅርስ ጥገና ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ትልቅ ፈተና መኾኑን እና ችግሩን ለመቅርፍ የሥልጠና አማራጮችን ማስፋት ላይ ትኩረት መደረጉን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሀገር ባለውለታው ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት(ንጉሥ ጎጃም ወከፋ)!
Next articleዓመታዊ የአምባሳደሮች ስብሰባ መካሄድ ጀመረ።