በአዲስ አበባ የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ከጸጥታ ችግር ነጻ ኾኖ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ እንደኾነ የከተማዋ ሰላምና ጸጥታ አሥተዳደር ቢሮ ገለጸ።

36

አዲስ አበባ: ጥር 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ ከተማ የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ከጸጥታ ችግር ነጻ ኾነው እንዲከበሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ እንደኾነ የከተማዋ ሰላምና ጸጥታ አሥተዳደር ቢሮ ገልጿል። በዓላቱ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ የከተማዋ የጸጥታ መዋቅር የሥራ ኀላፊዎች ውይይት አካሄደዋል።

የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱን እና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር መላው ማኅበረሰብ ከጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት የድርሻውን እንዲወጣ የከተማው የሰላምና ጸጥታ አሥተዳደር ቢሮ ኀላፊ ሊዲያ ግርማ ጠይቀዋል።

የአደባባይ በዓላትን ሽፋን በማድረግ ከተማዋን የብጥብጥ እና ሁከት ማዕከል በማድረግ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ክትትል እና የእርምት እርምጃዎች መውሰድ አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል

አዲስ አበባ የሰላም ተምሳሌት የኾነችበትን የአደባባይ በዓላት ቀደም ሲልም በሰላም አከናውና ማጠናቀቋን የተናገሩት ወይዘሮ ሊዲያ ይህንን በጥምቀት በዓልም መድገም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ከሚተላለፋ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ቀድሞ መሠራት እንዳለበትም ኀላፊዋ ገልጸዋል። አደባባይ ላይም ኾነ ሌሎች አካባቢዎች ላይ የሚወጡ ማንኛውም የህትመት ውጤቶች ከሃይማኖታዊ ይዘት የወጣ መኾን እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ ሰላምና ጸጥታ የሥራ ኀላፊዎች በከተማዋ ለግጭት መነሻ የኾኑ ጉዳዮችን ቀድሞ በመለየት ሰፊ የዝግጅት ሥራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለሁከት እና ብጥብጥ ስጋት ናቸው ተብለው የተለዩ ጉዳዮች ላይ ከሃይማኖት መሪዎች እና ከሃይማኖታዊ አደረጃጀቶች ጋር በመኾን ችግሮችን ለመፍታት አስቀድመው እንደሚሠሩም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በከተማዋ የጸጥታ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎችን ቀድሞ መለየት እና የሃይማኖት አባቶችን እንዲሁም ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሠራ ተገልጿል።

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት በዓል በማድመቅ፣ ያላንዳች የጸጥታ ችግር በማክበር እና በማስከበር ሂደትም በተለይ ወጣቶች ሚናቸው የላቀ በመኾኑ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

በዓሉን ተገን በማድረግ ሊፈጸሙ የሚችሉ የደንብ መተላለፍ እንዳይኖር እየተሠራ እንደኾነም የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ገልጿል።

ዘጋቢ፡- ዳንኤል መላኩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ የኢነርጂ ተጠቃሚነቷን ለማስፋት የተለያዩ አማራጮችን እየተከተለች እንደምትገኝም የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ድኤታ ነመራ ገበየሁ (ዶ.ር) ገለጹ፡፡
Next articleየሀገር ባለውለታው ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት(ንጉሥ ጎጃም ወከፋ)!