ኢትዮጵያ የኢነርጂ ተጠቃሚነቷን ለማስፋት የተለያዩ አማራጮችን እየተከተለች እንደምትገኝም የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ድኤታ ነመራ ገበየሁ (ዶ.ር) ገለጹ፡፡

15

አዲስ አበባ: ጥር 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የኢነርጂ ተጠቃሚነቷን ለማስፋት የተለያዩ አማራጮችን እየተከተለች እና እየተጠቀመች እንደምትገኝም የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ድኤታ ነመራ ገበየሁ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡

“የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ዘላቂ ዕድገትን የምታረጋግጥ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ የኢፌዴሪ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ የእድገት ማዕከል (IGC) ጋር በመተባበር በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ድኤታ ነመራ ገበየሁ (ዶ.ር) በንግግራቸው የአየር ንብረት ለውጥ አብዛኛውን የኢትዮጵያን ሕዝብ እየጎዳ በመኾኑ መንግሥት እንዴት ይህን ችግር መቅረፍ ይችላል በሚለው ጉደይ ላይ ውይይት በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡ ዶክተር ነመራ ከዓለም አቀፍ የእድገት ማዕከል (IGC) በግብርና እና በአረንጓዴ ማልበስ (አረንጓዴ አሻራ) ጋር ተያያዥነት ያለው ጥናት ያዘጋጀ እና ሀገሪቱ የጀመረችውን ጉዞ የሚያጠናክር ጥናት በመኾኑ ውይይት ለማድረግ የተዘጋጀ መድረክ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ የኢነርጂ ተጠቃሚነቷን ለማስፋት የተለያዩ አማራጮችን እየተከተለች እና እየተጠቀመች እንደምትገኝም ጠቁመዋል፡፡ ይህንም ለማጠናከር ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እየወሰደች መኾኑን ሚኒስትር ድኤታው ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ የዓለም አቀፍ የእድገት ማዕከልን የጥናት ውጤት ያቀረቡት የዋርቪክ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ስቴፋኖ ካሪያ በማደግ ላይ ባሉ እና ቀጣይነት ያለው ዕድገትን በማስመዝገብ ላይ ባሉ ሀገራት ላይ ያሉ ሶስት እውነታዎችን አቅርበዋል።

👉 በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የኑሮ ደረጃን ከፍ ለማድረግ እና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስመዝገብ አንገብጋቢ ፍላጎት እንዳላቸው

👉 በአየር ንብረት ለውጥ ታዳጊ አገሮች ትልቁን ሸክም እንደሚሸከሙ እና

👉 በማደግ ላይ ያሉ አገራት የወደፊት የልህቀት መጠን በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚያድግ ባቀረቡት የጥናት ውጤት አንስተዋል።
ዓለም አቀፍ የእድገት ማዕከል (IGC) የፕላኔቷን እና የዜጎችን ጤና በሚጠብቅ መልኩ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ዘላቂ የዕድገት መንገድን የሚዳስስ የኢኮኖሚ፣ የልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ፈጠራ ላይ እየሠራ የሚገኝ ተቋም ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአስገዳጅ የጥራት ደረጃዎችን ማጽደቁን የኢትዮጵያ ጥራት ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
Next articleበአዲስ አበባ የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ከጸጥታ ችግር ነጻ ኾኖ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ እንደኾነ የከተማዋ ሰላምና ጸጥታ አሥተዳደር ቢሮ ገለጸ።