
አዲስ አበባ: ጥር 3/2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥራት ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በ38ኛው ብሔራዊና የደረጃዎች ምክር ቤት 385 የጥራት ደረጃዎችን ማጽደቁን ገልጿል።
ተቋሙ 233 አዲስ እና 152 ነባር የጥራት ደረጃዎችን ማጽደቁን ነው በሰጠው መግለጫ የገለጸው።
ከእነዚህ ውስጥ 12ቱ አስገዳጅ ደረጃዎች መኾናቸውን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ (ዶ.ር) አስገንዝበዋል።
በተለይም ከውጭ ገብተው ለማኅበረሰቡ የሚቀርቡ የዘይት እና የስንዴ ምርቶች የበለፀጉና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲኾኑ ታሳቢ ተደርጎ አስገዳጅ ደረጃዎች እንዲወጣላቸው መደረጉንም ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
ብሔራዊ የበለፀገ ምግብ ምልክትንም ተቋሙ አስተዋውቋል። አምራቾች በምርቶቻቸው ላይ ምልክቱን እንዲጠቀሙ ይደረጋልም ተብሏል፡፡ ሸማች ማኅበረሰቡም የጥራት ደረጃ ምልክት ያለባቸውን ምርቶች ብቻ እንዲጠቀም ጥሪ ቀርቧል።
ዛጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!