ናኦሚ ግርማ የአሜሪካ የ2023 የምርጥ ተጫዋቾችን ሽልማት አሸነፈች፡፡

24

ባሕር ዳር: ጥር 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለሳን ዲያጎ ዌቭ የሴቶች ቡድን እየተጫወተች የምትገኘው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ የአሜሪካ የ2023 የሴቶች ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን አሸንፋለች፡፡

በዚህም የ23 ዓመቷ ናኦሚ በአሜሪካ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያዋ ተከላካይ እና ሁለተኛዋ ጥቁር የዓመቱ ምርጥ ሴት ተጫዋች ሽልማት አሸናፊ መኾን ችላለች፡፡

ናኦሚ የአሜሪካ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ2023 ባደረጋቸው 16 የፊፋ የሴቶች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ የቡድኑን የተከላካይ ክፍል በብቃት መምራቷ ተገልጿል፡፡

ከሽልማቱ በኋላ ናኦሚ “ሽልማቱን በማሸነፌ ደስ ብሎኛል፤ ከዚህ ሽልማት ጀርባ ሌሎች የቡድን አጋሮቼ ቁልፍ ሚና ነበራቸው፤ ያለፈው ዓመት ለእኔ እና ለብሔራዊ ቡድኑ ታሪካዊ ዓመት ነበር” ብላለች፡፡

የምርጥ ተጫዋች ምርጫው ከአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ ከእግር ኳስ ዳይሬክተሮች የቦርድ አባላት፣ ከብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ሊግ ዋና አሠልጣኞች፣ ከሚዲያ አባላት እና ከአሥተዳዳሪዎች በተሰጠ ድምፅ የተወሰነ መኾኑ ተመላክቷል፡፡ ናኦሚ ከፈረንጆቹ 2021 ጀምሮ በአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን የተካላከይ ስፍራ ላይ እየተጫወተች መኾኑም ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዚህ ዓመት የተፋሰስ ልማት ከ31 ሺህ 200 ሔክታር በላይ መሬት እንደሚለማ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡
Next articleአቶ ደመቀ መኮንን ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን መስራች እና ሊቀ መንበር ቢል ጌትስ ጋር ተወያዩ።