
ባሕር ዳር፡ ጥር 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በመንግስታት ቅብብሎሽ ተጠብቆ የዘለቀውን የዲፕሎማሲ ስራ በጽናት ማስቀጠል ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተው የዲፕሎማሲ ሳምንት አካል የሆነው የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በየዘመኑ ወሳኝ ቦታ ይዞ ኖሯል።
ኢትዮጵያውያን ነጻነታቸውን አስከብረው ለመኖር፣ በትምህርትና በሳይንስ እድገት ለማሳየት፣ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ግንኙነትና ትብብር ለማሳደግ የዲፕሎማሲ መንገድ ተከፍቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአለም መድረክ ያስመዘገበቻቸውን የዲፕሎማሲ ስኬቶች በመዘርዘር በአለም መድረክ በመንግስታት ማህበር አባልነትና በተባበሩት መንግስታት ምስረታ ንቁ ተሳትፎ ማድረጓን አስታውሰዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ በየዘመኑ በነበሩ መንግስታት ቅብብሎሽ ተጠብቆ የኖረው የዲፕሎማሲ ስራ በጽናት መዝለቅ ይኖርበታል ብለዋል። አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የውጭ ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮሩ “የዲፕሎማሲ ዜና መዋዕል” እና “የዘመናዊት ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ከ1900 እስከ 2015 ዓ.ም” የሚሉ ሁለት መጽሀፍትን በዚሁ ወቅት መርቀዋል።
“የዲፕሎማሲ ዜና መዋዕል” መጽሀፍ የኢትዮጵያ ነገስታቶች የመከሯቸውንና ሌሎች ክንውኖችን የያዘ ነው። የዘመናዊነት ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ መጽሀፍ ከ1900 እስከ 2015 በተለያየ ቦታ የነበሩ የውጭ ግንኙነት ጽህፎችን፣ ስምምነቶችን በአንድ መጽሀፍ ተሰንዶ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረቡበት ነው።
እየተካሄደ ባለው የፓናል ውይይት የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ የሚዳስሱ ፅሁፎች በምሁራንና የዘርፉ ሊሂቃን ቀርበው ውይይት እንደሚደረግ በመድረኩ ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!