
ባሕር ዳር: ጥር 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባዔ ትናንት ሲካሄድ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ያጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች በርካታ ጉዳት እያደረሱ መኾኑንና ለመፍትሔው የሰላም ሚኒስቴር አበክሮ ሊሠራ እንደሚገባ ተነስቷል።
ችግሮቹ በውይይት መፈታት እንዳለባቸውና የሰላም ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ኀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል። በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በርካቶች ላይ ጉዳት ያስከተሉ ግጭቶች መኖራቸውን አንስተው፤ ግጭቶቹ በሰላማዊ መንገድ ተፈትተው ኀብረተሰቡ ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለስ በአግባቡ መሥራት እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል።
በግጭቶቹ ሳቢያ በርካታ ንጹሃን በመፈናቀላቸው ለችግር መዳረጋቸውን የምክር ቤት አባላት ጠቁመዋል። የሀገርና የሕዝብ ንብረት እየጠፋ ከመኾኑም በላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዋጋ እየከፈለ በመኾኑ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መሥራት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ መንግሥት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በሰላማዊ ውይይቶች ለመቅረፍ ዝግጁ መኾኑን ገልጸዋል። በክልሎቹ ያለው ግጭት በሰላማዊ ውይይቶች ለመቅረፍ በመንግሥት በኩል ጥረቶች እየተደረጉ መኾናቸውን ጠቅሰው በጦርነት የትኛውንም የሀገሪቱን ችግሮች መቅረፍ አይቻልም ሲሉ ጠቁመዋል።
የጦርነት መቋጫው ሰላማዊ ንግግር እና ውይይት በመኾኑ በአማራና ኦሮሚያ ክልል ያሉ ታጣቂዎች ተጨማሪ ዋጋ ሳይከፈል ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ መጠየቁን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ውይይት ሊመጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በሀገሪቱ ባለፉት አምስት ዓመታት የነበሩ ችግሮች ምክንያታቸውና የተፈቱበት መንገድ በጥናት እንዲረጋገጥና እንዲለይ መደረጉንም ጠቅሰዋል። በተለይም የወሰን፣ ማንነት፣ የአሥተዳደራዊ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ የመልካም አሥተዳደርን ጨምሮ የሀብት ክፍፍልና የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን አስረድተዋል።
ኢፕድ እንደዘገበው የፖለቲካ ባሕል አለመዳበርና ከታሪክና ትርክት ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮች ለሀገሪቱ የሰላም እጦትና የግጭት መበራከት ምክንያቶች ስለመኾናቸውም አቶ ብናልፍ ጠቁመዋል።
በጥቂት ፖለቲከኞች አለመረጋጋትና የሥልጣን ፍላጎት የተነሳ ሕዝብ እየተሰቃየ የሚሄድበት ኹኔታ ሊቆም ይገባል ያሉት አቶ ብናልፍ፤ ከመገዳደል ወደ መወያየት መምጣት የሚያስችል የፖለቲካ ባሕልን ማዳበር ያስፈልጋል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!