
ባሕር ዳር: ጥር 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወንጪ ሁሌም ንፁህ የተፈጥሮ ስጦታ ሆና ቆይታለች ብለዋል። የተፈጥሮን ድንቅ በረከት ተቀብሎ ተንከባክቦ እና አበልፅጎ መጠቀም ደግሞ የኛ የሰው ልጆች ተጠባቂ ተግባር መኾኑንም ነው የገለጹት።
የወንጪ ዳንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንደርን በማልማት ሂደት በግንባታው ምዕራፍ ከ8 ሺህ እስከ 12 ሺህ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ገልጸዋል። ግዙፍ የመሰረተ ልማት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። 43 ኪሎ ሜትር መንገዶች፤ 35ኪሎ ሜትር የመንገድ መብራት እና የኃይል አቅርቦት፤ 72 ሜትር ድልድይ እና ትምህርት ቤት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት የአካባቢው ወጣቶች ታላላቅ የልማት ሥራዎች ይዘው የሚመጡትን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማጣጣም ጀምረዋል። ሰፊው የአካባቢው ማኅበረሰብም አሁን የላቀ የተጠቃሚነት ዕድል አግኝቷል ብለዋል በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልእክት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!