“የዳታ ልማት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ ጉዳይ በመኾኑ በትብብር ልንሠራበት የሚገባ ታላቅ ሀብት ነው” የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

31

ባሕር ዳር: ጥር 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ጉዳዮች ክፍል ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የዳታ ልማት እና አሥተዳደር ረቂቅ መመሪያ ላይ የባለድርሻ አካላት፣ መሪዎች እና ተወካዮች በተገኙበት ውይይት ተካሄዷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከዳታ ልማት ውጭ የሚታሰብ አለመሆኑን በማውሳት የዳታ ልማት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ አስቻይ በመኾኑ በትብብር እና በርብርብ ልንሠራበት የሚገባ ታላቅ ሀብት ነው ብለዋል።

የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን የማስተባበር ኀላፊነት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ቢወስድም ለስኬታማነቱ ግን ሁሉም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በቅንጅት ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ከትብብር መስኮቹ አንዱ የዳታ ልማት መኾኑን ተናግረዋል። የዳታ ልማትን በተገቢው ደረጃና ሂደት ለመምራት መሰል መመሪያዎች እንደሚያስፈልጉ ገልፀዋል።

የመመሪያው ዓላማም በተቀናጀ አግባብ እና በትብብር መንፈስ ውድ የኾነውን የዳታ ሀብት ለማልማት የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ሁሉ የሚተባበሩበትን እና በቅንጅት ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን የሚሠሩበትን መድረክ ለመፍጠር እንደኾነ አመላክተዋል።

መመሪያውን ወደ ቀጣይ የማፀደቅ ሂደት በመውሰድ በአጭር ጊዜ ወደ ትግበራ ለማስገባት እንደሚሠራ ገልፀዋል። በውይይት መድረኩ የተገኙት በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ክፍል ተወካይ ዋይ ሚን ክዎክ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የዳታ ልማት እና አሥተዳደር ላይ እየሠራቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል። በቀጣይም በትብብር የሚሠሩ ሥራዎችን አጠናክረን እናስቀጥላለን ነው ያሉት።

በመድረኩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ እቅድ እና ልማት ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት፣ የስፔስ ሳይንስ እና የጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የመረጃ መረብ ደኅንነት አሥተዳደር፣ የብሔራዊ መታወቂያ፤ እና የኢሚግሬሽን እና የዜግነት ጉዳዮች አገልግሎቶች ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡

የመመሪያውን አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ ያወሱት ተሳታፊዎች መመሪያው በፍጥነት ወደ ትግበራ እንዲገባም ጥሪ ማቅረባቸውን ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም መድረክ ድረስ” የተሰኘ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማሲ ፎረም ተከፈተ።
Next article“የተፈጥሮን ድንቅ በረከት ተቀብሎ ተንከባክቦ እና አበልፅጎ መጠቀም የኛ የሰው ልጆች ተጠባቂ ተግባር ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)