
ባሕር ዳር፡ ጥር 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 675 ተጠርጣሪዎችን በሦስት ዙር የተሃድሶ ሥልጠና በመስጠት ወደ ኅብረተሰቡ መቀላቀሉን የባሕር ዳር ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በባሕር ዳር ማረሚያ ቤት የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን በመጎብኘት ከኮማንድ ፖስቱ አመራሮች ጋርም ተወያይቷል፡፡
በጉብኝቱ በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ በመልካም ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን አረጋግጠዋል። የባሕር ዳር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሜጀር ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሱ፤ በኮማንድ ፖስቱ በወንጀል ተጠርጥረው ወደ ማረሚያ ቤት የሚገቡ ተጠርጣሪዎች መልካም ስብዕና ይዘው እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በሦስት ዙር የተሃድሶ ሥልጠና 675 ተጠርጣሪዎች ወደ ሕብረተሰቡ መቀላቀላቸውን ጠቅሰው፤ በርካቶችም የምክር አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በቅርቡ ለሚሰጠው አራተኛ ዙር የተሃድሶ ሥልጠና 227 ተጠርጣሪዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ በቆይታቸው የሰብዓዊ መብት አያያዙ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ብለዋል።
የኮማንድ ፖስቱ አባል ዋና ኢንስፔክተር አለማው አያሌው፤ የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ከተሳሳተ መንገድ ወጥተው ወደ መደበኛ ሥራቸው ለሚመለሱት ሁሉ አስፈላጊው ትብብር እየተደረገ መሆኑም ተናግረዋል፡፡
መልካም ዜጋ ሆነው በአገራቸው ልማት ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑም አስፈላጊው የግንዛቤና ምክር አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል። ተጠጣሪዎቹ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት በባህርዳር ማረሚያ ቤት ለአራተኛ ዙር የተሃድሶ ሥልጠና የተዘጋጁ ተጠርጣሪዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም አያያዝ መኖሩን ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ አባላት ተጠርጣሪዎች ከጥፋት ታርመውና መልካም ስብዕና ይዘው እንዲወጡ በማድረግ ላደረጉላቸው አስተዋፅዖ አመስግነዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አዝመራው አንዴሞ፤ በጉብኝቱ የተጠርጣሪዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ በመልካም ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል።
በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የመርማሪ ቦርዱ አባላት በነበራቸው ጉብኝት ተጠርጣሪዎችን በማነጋገር ያሉበትን ሁኔታም በግልፅ መረዳታቸውን ተናግረዋል። በባህርዳር ማረሚያ ቤት የሚገኙ በርካታ ተጠርጣሪዎች የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ሕብረተሰቡ መቀላቀላቸውንም በተግባር አረጋግጠናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባላት በትናትናው ዕለት ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጋር በነበራቸው ውይይት የተጠርጣሪዎች አያያዝ በመልካም ሁኔታ ላይ ስለመሆኑ ገልፀውላቸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!