በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ ያለልዩነት እንደሚደግፍ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።

53

ባሕር ዳር: ጥር 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ ይፋ ባደረገው መግለጫ በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ በተመለከተ፣ በስምምነቱ ይዘትና ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ ባሉት እድሎችና ስጋቶች ላይ አባላቱ በዝርዝር በመወያየት ለውጤታማነቱ የድርሻቸውን ለመወጣት መወሰናቸውን አስታውቋል።

አያይዘውም መንግስት ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መላው ኅብረተሰብ የበኩላቸውን አውንታዊ ሚና እንዲወጡ ጥሪ ማቅረቡንም በመግለጫው አመልክቷል።

የመግለጫው ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ👇

እኛ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጥር 01፣ ቀን 2016 ዓ.ም በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ የተገኝን የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ከተማ ባካሄድነው ስብሰባ :

1ኛ በኢትዮጵያና በሶማሌ ላንድ መካከል የተፈረመውን ” መግባቢያ ሰነድ” በተመለከተ የስምምነቱን ማዕቀፍ ፣ዝርዝር ይዘቱን እና ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ ባሉት እድሎችና ስጋቶች ላይ በዝርዝር ከተወያየን በኋላ ስምምነቱን ያለልዩነት የምንደግፍ መሆናችንን አረጋግጠናል::ከተግባራዊነቱ አንፃር የሚኖሩትን ውስጣዊ እና ውጫዊ ስጋቶችን እና እድሎችን በዝርዝር መክረን ለስምምነቱ ውጤታማነት በጋራ በመቆም ሚናችንን ለመወጣት ያለንን ቁርጠኝነት ዳግም እናረጋግጣለን:: መንግስት ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መላው ህብረተሰባችን የበኩላቸውን አውንታዊ ሚና እንዲወጡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን::

2ኛ. አካታች ሀገራዊ ምክክርን በተመለከተ ስራው የደረሰበትን ደረጃ ፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን እና በመፍትሄ አቅጣጫወች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናን አስመልክቶ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በቀረበው ሪፓርትና ማብራሪያ ላይ ውይይት ካደረግን በኋላ ለምክክሩ ውጤታማነት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን በመፍታት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ አጠናክረን ለመቀጠል ተስማምተናል:: በሂደቱ ሁሉም የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉም ጥሪያችንን እናቀርባለን:: ለምክክር ኮሚሽኑ ተልዕኮ ስኬት እንቅፋት እየሆነ ያለውን የሰላምና የጸጥታ ችግር በመቅረፍ መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መላው ህዝባችን እንዲረባረቡ ጥሪ እናቀርባለን::

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ

ጥር 02 ፣ 2016 ዓ/ም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥሪ የተደረገላቸው የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ነው” ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።
Next article675 ተጠርጣሪዎችን በሦስት ዙር የተሃድሶ ሥልጠና በመስጠት ወደ ኅብረተሰቡ መቀላቀሉን የባሕር ዳር ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።