“ጥሪ የተደረገላቸው የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ነው” ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።

70

አዲስ አበባ: ጥር 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ለሁለተኛ ዙር ጥሪ የተደረገላቸውን ዲያስፖራዎች በሚመለከት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መገሰለጫ ሰጥቷል። ከሀገራቸው ለረጅም ዓመታት ተነጥለው የቆዩ እና በውጪ ሀገር ተወልደው ስለ ሀገራቸው እውቅና የሌላቸው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁለተኛው ትውልድ በሚል ጥሪ መደረጉን ሚኒስትር ድኤታዋ ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል።

በጥሪው መሰረትም አሁን ላይ ወደ ሀገራቸው እየገቡ እና በአየር መንገድ በመገኘት አቀባበል እየተደረገላቸው ነው ተብሏል። ቆይታቸውን ሰላማዊ ለማድረግም አዲስ አበባ ከተማን ሰላም እና ደህንነቱን ለማስጠበቅ በከተማው የተለያዩ የጸጥታ ማስከበር ሥራዎች እየተሰሩ መኾኑን ሚኒስትር ድኤታዋ አንስተዋል።

የዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተሩ ሙሀመድ እንድሪስ (ዶ.ር) በበኩላቸው በተለያየ ምክንያት ከሀገራቸው ተለይተው የቆዩ እና በዚያ ተወልደው ስለ ሀገራቸው ለማያውቁ ወጣቶች ሁሉ መጥተው እንዲጎበኙ ጥሪ መደረጉን አንስተዋል፡፡ ከሀገሩ የተነጠለ ትውልድ እንዳይኖር በስፋት እየተሠራ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

ትውልዱን ከሀገሩ ጋር የማስተዋወቅ እና ከሀገሩ ጋር የማስተሳሰር መርሐ ግብርም የሁለተኛው ትውልድ በሚል ለሁለተኛ ጊዜ የተጠሩ ወገኖች ናቸው እየገቡ ያሉት።
ከሀገራቸው ጋር የሳሳ ግንኙነት ያላቸው እና ባሉበት ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች ረጅም ጊዜያትን ያሳለፉ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ናቸው በጥሪው መሠረት እየገቡ የሚገኙ፡፡

መሰል ሥራዎች ተጠናክረው ሲቀጥሉም ስለ ሀገሩ ጥብቅና የሚቆም እና ስለ ሀገሩ ጥቅም እና ጉዳት የሚገድደው ትውልድ ለመፍጠር ያግዛል ተብሏል። በዚህ ጥሪ የመጡ እንግዶችን ሁሉ ቆይታ ለማሳመርም ዐብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ በስፋት እየተሰራ ይገኛል ተብሏል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታው ስለሺ ግርማ በበኩላቸው ወደ ሀገራቸው የሚመጡ ሁሉ ብዝኀ ባሕላቸውን እንዲያውቁ፣ ታሪካዊ መሠረታቸውን እንዲረዱ፣ አሻራቸውን እንዲያኖሩ እና እረፍታቸውን በለገራቸው እንዲያጣጥሙ ታልሞ በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህ የቆይታ ጊዜያቸውም የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶችን እንዲያጣጥሙ፣ የኢትዮጵያን እደ ጥበቦች እንዲጎበኙ፣ እንዲተዋወቁ እንዲሁም የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሣሪያዎችን እና ኹነቶችን እና የባሕል አልባሳትን እንዲረዱ ይደረጋል ተብሏል።

ከዚህ ኹነት በኋላ የጉብኝት መርሐ ግብር መዘጋጀቱን ያነሱት ሚኒስትር ድኤታው በዚህ ዘርፍ በሆቴል እና በአየር መንገድ በኩል የዋጋ ቅናሽ ተደርጎላቸዋል ብለዋል። ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ስለ ሀገራቸው ምርት እንዲያውቁም “የኢትዮጵያን ይግዙ” የተሰኘ ባዛር ተዘጋጅቶ የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ምርቶች ለግብይት እንዲቀርቡ ይደረጋል ተብሏል። በመጨረሻም የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት የሚያመላክቱ ዝርዝር ማስረጃዎች ተዘጋጅተው እንደሚቀርብ ተመላክቷል፡፡

ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው እባቡ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ100 ሚሊየን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ጋር ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰናል” የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን
Next articleበኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ ያለልዩነት እንደሚደግፍ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።