
ባሕር ዳር: ጥር 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከ11 የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ጋር ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።
ስምምነቱን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ እና ባለሀብቶች ተፈራርመዋል። ባለሃብቶቹ ኮርፖሬሽኑ ካሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል በአምስቱ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ገብተው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ነው የተፈራረሙት።
ሁለት ባለሀብቶች በባሕርዳር እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው መዋዕለ ነዋያቸውን ለማድረግ ሲስማሙ ሌሎች ደግሞ በመቀሌ፣ ጅማ እና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በእያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ኩባንያዎች እንደሚገቡ ተገልጿል።
ባለሃብቶቹ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በአልባሳትና ጨርቃጨርቅ፣ በመድኃኒት እንዲሁም በፕላስቲክ ማምረት ዘርፍ ይሰማራሉ ተብሏል። 11 ባለሀብቶች በድምሩ ከ100 ሚሊየን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ መኾናቸው ተገልጿል። 31 ሺህ ካሬ ሜትር የማምረቻ ሼድና 4 ነጥብ 5 ሄክታር የለማ መሬት ተረክበው ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሏል።
ስምምነት ከተፈራረሙት ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ናቸው፤ ከ50 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ዘላቂ የሆነ የገበያ ትስስርና 5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ የሥራ እድል የሚፈጥሩ መኾኑን ኤፍቢሲ ዘግቧል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ ስምምነቱ እነዚህ ባለሀብቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!