
ባሕርዳር: ታኅሳሥ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለዘመናት ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ከራሷ አልፎ ለአፍሪካውያን ብሎም ለጥቁር ሕዝቦች ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናግረዋል።
አቶ ደመቀ በቅኝ ግዛት ዘመን ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የጥቁር ሕዝብ ወኪል ኾና በሊግ ኦፍ ኔሽን መሳተፏን አውስተዋል። “ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካውያንና ለሌሎችም ጥቁር ሕዝቦች ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተች ናት” ሲሉም ተናግረዋል።
በቀደምት ዘመናት ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ መንገድ የውጭ ግንኙነት ታካሂድ እንደነበር አቶ ደመቀ አስታውሰው፤ ከ116 ዓመታት በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቋቁሞ ሥራው ተቋማዊ መደረጉን አንስተዋል።
በዛሬው ዕለት የሚከፈተው የዲፕሎማሲ ሳምንት ያለፉት ዓመታት የዲፕሎማሲ ጉዟችን ያሉንን ወረቶች ማየት፣ አሁን ላይ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያሉ ዕድሎችና ፈተናዎችን መለየት የሚሉ ዓላማዎችን አንግቦ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!